Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከ79 ሺህ በላይ ቤቶች በህገወጥ መንገድ መገንባታቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከ1 ሺህ 352 ሄክታር በላይ መሬት በህገወጥ መንገድ መያዙን እና ከ79 ሺህ በላይ ቤቶች ደግሞ በህገወጥ መንገድ መገንባታቸውን ጥናት አመለከተ።

ጥናቱ ከ1997 ወዲህ እና ከ500 ካሬ ሜትር በላይ በሆኑ መሬቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን በሪል እስቴት ስም በህጋዊነት ከተሰጣቸው ቦታ ውጪ መውረር እንዲሁም ለሌሎች ግለሰቦች ማስተላለፍ፣ ወደ መሬት ባንክ የገቡ እና ለአረንጓዴ ስፍራ ተብለው የታጠሩ ቦታዎችን በቡድን፣ በግለሰቦች እንዲሁም በባለሀብቶች ማስወረር እንደተስተዋሉ አመልክቷል።

ከህገወጥ የመሬት ወረራ እና ግንባታ ችግሮችን ለማጥራት ሲካሄድ የነበረው የጥናት ግኝት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፥ በከተማዋ መሬት አንዱና ዋነኛው ሀብት በመሆኑ በመረጃ እና በስርዓት ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በከተማዋ በመሬት ላይ የሚደረገው ህገወጥ ተግባራት ለስራ እድል ፈጠራ እና ለፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲሁም በአጠቃላይ የከተማዋ እድገት ማነቆ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል ።

በቅርቡ በአስሩም ከፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች በተካሄደው ከህገወጥ የመሬት ወረራ እና ግንባታ ችግሮችን ለማጥራት የጥናት ግኝት መሰረት በ632 ቦታዎች ከ1 ሺህ 352 ሄክታር በላይ መሬት በህገወጥ መንገድ መያዙን ግኝቱ አመላክቷል።

በተጨማሪም 79 ሺህ 112 ቤቶች በህገወጥ መንገድ መገንባታቸውን በጥናቱ ተመላክቷል።

በሪል ስቴት ስም በህጋዊነት ከተሰጣቸው ቦታ ውጪ ሌላ ቦታ መውረር እና ማስፋፋት እንዲሁም ለሌሎች ግለሰቦች ማስተላለፍ ወደ መሬት ባንክ የገቡ እና ለአረንጓዴ ስፍራ ተብለው የታጠሩ ቦታዎችን በቡድን፣ በግለሰቦች እንዲሁም በባለሀብቶች መሬት የማስወረር ዝንባሌዎች እንደሚስተዋሉ ተገልጿል ።

በተጨማሪ በእምነት ተቋማት ስም፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች እና ማስፋፊያ አካባቢዎች በከተማ ግብርና ስም መሬት መውረር እና ግንባታ ማካሄድ፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተብለው የተወሰዱ ቦታዎችን ለግለሰቦች ማስተላለፍ እንዲሁም በመሀል ክፍለ ከተሞች የመንግስት ቤቶችን በማፍረስ ለግለሰቦች ካርታ የማድረግ ህገወጥ ተግባራት ተፈጽመዋል።

የአርሶ አደሮችን መሬቶች  በርካሽ ዋጋ የመግዛት፣ የመሬት ደላሎች ከባለሀብቶች እና ከመንግሥት  አካላት ጋር በመመሳጠር  እና የመሬት ማኔጅመንት አሰራሮችን በመጣስ መሬት መውረር እና ቤቶችን መገንባት እንደሚስተዋል በጥናት ግኝቱ ተገልጿል ።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ማጠቃለያ የተወረረው መሬት ለጥቂት ህገወጦች በአቋራጭ መክበሪያ መሆንን ገልጸው፤ ይህም የተፈጥሮ ሀብት ለዜጎች ተጠቃሚነት እንዳይውል ማነቆ መሆኑን ገልጸዋል ።

የጋራ ሀብት መጠቀሚያ የሆነውን መሬት በህገወጥ መንገድ የያዙ አካላት ላይ አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ እና በወረራ የተያዙ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ የመመለስ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል ።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው፥ የመሬት ዘርፍ የከተማዋን እድገት እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የከተማዋን ገጽታ ከማበላሸቱ ባለፈ የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ አመራሮች እና መላው ነዋሪዎች መንግስት ለሚወስደው እርምጃ ተባባሪ እና የርብርብ ማዕከል እንዲሆን አቶ መለሰ ገልፀዋል።

የቀረበውን የጥናት ግኝት በተመለከተ ከከተማ አስተዳደሩ እና ከፌደራል ተቋማት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የተለያዩ ሀይማኖት ተቋማት ተወካዮች የመሬት ወረራ መንስኤ እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት  ማካሄዳቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክረተሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.