Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣መስከረም 14፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን የፀጥታ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
 
ዝግጅት ከመደረጉም ባሻገር ለፀጥታ ኃይሉ በበጎ ፈቃደኝነት አጋዥ የሆኑ በቅርቡ የተመረቁ ከ27ሺህ በላይ ወጣቶች በፀጥታው ሥራ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ዝግጅት ተደርጓል ተብሏል፡፡
 
ወደ መስቀል አደባባይ የሚመጡ የከተማው ነዋሪዎች የኮቪድ ፕሮቶኮልን ባሟላ ሥነ-ሥርዓት ተሳታፊ እንዲሆንም ፖሊስ አሳስቧል፡፡
 
በሌላ በኩል በዓሉ በሰላም እንዲከበር ለማስቻል በህገ መንግስቱ እውቅና የሌላቸው ባንዲራዎች ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ መልዕክቶችንና አርማዎችን በዓሉ በሚከበርባቸው ቦታዎች ላይ ይዞ መገኘት የተከለከለ መሆኑም ተገልጿል፡፡
 
የአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት የሚያከናውነውን ተግባር በመደገፍ የከተማው ነዋሪዎች የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን ÷ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመረጃ ስልኮች 011-1 11-01-11 ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 መረጃ መስጠት እንደሚቻል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
 
የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠርም ለአሽከርካሪዎች ዝግ የሚሆኑ መንገዶች የሚኖሩ ሲሆን ÷አሽከርካሪዎች ተገንዝበው ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል ፡፡
 
በዚህም መሰረትከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር ኦሎምፒያ አደባባይ አከባቢ፤ከመገናኛ ፣ በሃያ ሁለት ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድሃኒያለም፤ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያ አካባቢ፤ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ባሻወልዴ ችሎት ወይም ፓርላማ መብራት፤ ከፒያሣ አካባቢ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቸርችር ጎዳና ቴዎድሮስ አደባባይ፤ ከተክለ ሀይማኖት በሜትሮሎጂ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት አካባቢ
 
እንዲሁም ከተክለ ሀይማኖት ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚወስደው መንገድ ጥቁር አንበሳ የኋላ በር አካባቢ፤ ከሲኒማ ራስ በጎላ ሚካኤል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኢምግሬሽን የኋላ በር መግቢያ፤ከጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ፣ ብሄራዊ ቲያትር የሚወስደው መንገድ ጎማ ቁጠባ፤ ከባሻ ወልዴ ችሎት በኦርማ ጋራዥ ወደፉል ውኋ መስኪድ የሚወስደው መንገድ ንግድ ማተሚያ ቤት ፤ከጎፋ በቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ ወደ ለገሐር አዲሱ መንገድ የመወስደው መንገድ ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ መስቀለኛው ላይ፤ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ሜክሲኮ አደባባይ
 
በተጨማሪ ከሳሪስ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የቀድሞ አራተኛ ክፍለጦር አካባቢ መንገዱ የሚዘጋ ሲሆን ይለፍ ለሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ መሆኑ ታውቋል፡፡
 
ደመራው የሚደመርበት መስቀል አደባባይ እና ከቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ስታዲዬም እንዲሁም ከሃራምቤ ሆቴል ወደ ሴንጅ ዮሴፍ የሚያቋርጠው መስቀለኛ መንገዱ ለበዓሉ በሚደረገው ዝግጅት ምክንያት ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ዝግ የሚደረግ ይሆናል፤በተጨማሪም ከሳሪስ እና ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ከባድ ተሸከርካሪዎች መንገዱ አጎና ሲኒማ ጋር የሚዘጋ ይሆናል ነው የተባለው፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.