Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የ2013 ተቀዳሚ ጉዳይ ነው- ኢ/ር ታከለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የ2013 በጀት አመት ተቀዳሚ ጉዳይ እንደሚሆን ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ።

በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ስር ለሚገኙ ተቋማት ከፍተኛ ባለሙያዎች ለሶሰት ቀናት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

ስልጠናው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያየዘ ነው በቀጣይ ጊዜያት ታችኛዉ መዋቅር ድረስ እንደሚቀጥል የከተማዋ ከንቲባ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በተያዘው በጀት ዓመት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ እንከኖችን ማረም ለነገ የማይባል ዋነኛ ተግባር ነዉ ብለዋል።

ለነዋሪዎች የሚሰጠው አገልግሎት መጠነኛ መሻሻሎችን እያሳየ ቢሆንም ከዚህ በላይ መስተካከል እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

ለዚህም በፐብሊክ ሰርቪስ መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችና አመራሮች ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ነው ያነሱት።

ኢንጂነር ታከለ እያንዳንዱ ባለሙያ በቀጣይ አመት “እራሱን በተገልጋዩ ሕብረተሰብ ጫማ ውስጥ ሆኖ በማየት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀት ይገባል” ብለዋል።

እንደ አስተዳደሩ መረጃ በከተማዋ ከ130 ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ይገኛሉ።

ከትምህርት፣ከጤና እና የፀጥታ ተቋማት ውጪ ያሉ 65 ሺህ የሚሆኑ የከተማዋ መንግሥት ሠራተኞች በቀጣይም በተመሳሳይ ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ስልጠና እንደሚወስዱም ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.