Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎች፣ የተለያዩ ድርጅቶች እና ኢንዱስትሪዎች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች፣ የተለያዩ ድርጅቶች እና ኢንዱስትሪዎች ሰላምን ሊያውኩ ከሚችሉ ማናቸው ዓይነት ተግባራት ነጻ እንዲሆኑ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ተጠይቋል፡፡
ዛሬ በከተማዋ ከሚገኙ ሆቴሎች፣ የተለያዩ ድርጅቶች እና ኢንዱስትሪዎች አሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ተወካዮች ጋር በወቅታዊ የሀገር ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች፣ የተለያዩ ድርጅቶች እና ኢንዱስትሪዎች ሰላምን ሊያውኩ ከሚችሉ ማናቸው ዓይነት ተግባራት ነጻ እንዲሆኑ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ተጠይቋል፡፡
የከንቲባ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሺሰማ ገብረ ስላሴ ÷ ወቅታዊ የሀገሪቱን የጸጥታ ሁኔታን በመጠቀም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለይ ሆቴሎች፣ የተለያዩ ድርጅቶች እና ኢንዱስትሪዎች የጥፋት ኃይሉን ተልዕኮን ለማስፈጸም እና ሰላምን ሊያውኩ የሚችሉ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ ብለዋል፡፡
ተቋማቱ ለከተማዋ ኢኮኖሚ መንቀሳቀስ እና ተያያዥ ጉዳዮች ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ከማንኛውም ዓይነት የጸጥታ ችግር ነጻ ሆነው የየዕለት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ሺሰማ አስታውቀዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የሆቴሎች፣ የተለያዩ ድርጅቶች እና ኢንዱስትሪዎች አሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ተወካዮችም በበኩላቸው ÷ በስራ አካባቢዎች የተደበቁና የጥፋት ኃይሉን የህውኃት ቡድንን ሀገር የማፍረስ ዓላማን ለማሳካት የሚሯሯጡ ተላላኪዎችን በማጋለጥ መንግስት ከጀመረው ህግን የማስከበር እርምጃ ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል፡፡
ለዘርፎቹ ማደግ እና ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ሰላም ያስፈልጋል ያሉት የአሰሪ ተወካዮች÷ የጥፋት ኃይሉ ያቀዳቸውን ሴራዎች ማክሸፍ የሁሉም የዘርፉ ኃላፊነት በመሆኑ ለሰራተኞች ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በየተቋማቱ የተደበቁ ተላላኪዎችን በማጋለጥ ሰላምን ማስጠበቅ ይኖርብናልም ብለዋል፡፡
ከዚያም ባለፈ ለህግ ማስከበር ስራ ህይወቱን እየሰዋ ላለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በገንዘብም ሆነ በሌሎች ተግባራት አስፈላጊን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸዉን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ሞላ በወቅቱ እንደገለጹት ÷ ሀገርን በጨለማው ዘመን አስተሳሰብ የማስቀረት ዓላማ ያላቸውን ሴረኞች የኢንዱስትሪው ባለቤቶችና ባለሙዎች ሊታገሉ እንዲሁም መንግስት ከጀመረው ህግን የማስከበር እርምጃን ሊደግፉ እና ሊያግዙ ይገባል ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክሬተሪያት ጥህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.