Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት ከሪል እስቴት አልሚዎች ጋር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋን ማልማት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከግሉ ዘርፍ የሪል እስቴት አልሚዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ውይይት አካሂዷል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ያስሚን ውሀብረቢ ÷ የከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጃቸውን አማራጭ የቤት ልማት ሞዳሊቲዮችን ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ ለሪል እስቴት አልሚ ድርጅቶች እና ተወክለው ለመጡ ተሰብሳቢዎች አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷ ከሪል እስቴት አልሚዎች ጋር በመተባበር የመክፈል አቅም ያላቸውን ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ለማድረግና የሌላቸውን ሌሎች ነዋሪዎች ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ ተከራይተው የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ባለሐብቶች የልማት አጋር እንደመሆናችሁ መጠን የተዘጋጁ ሞዳሊቲዎችን በዝርዝር በመመልከት ለተግባራዊነቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩም ጥሪ ተላልፏል፡፡

አያይዘውም የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የቤት ፍላጎት በሂደት ለመቅረፍ አምስት የቤት ግንባታ ሞዳሊቲዎችን በዝርዝር አዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱ አጋርነታችሁን ይሻል ብለዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ በአጭር ጊዜ የቤት ግንባታ ማጠናቀቅ የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት የበኩላቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት ከንቲባዋ÷የውጭ ሀገር አልሚዎችን የአዋጭነት ደረጃ በመፈተሽ እንዲሳተፉ ለማድረግ ይሰራልም ብለዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሪት ያስሚን ውሀብረቢ÷የቤት አቅርቦትን በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በዓመት 200 ሺህ እና ከዚያ በላይ ቤቶችን መገንባት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡

በውይይቱ መጨረሻ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እና በቅርበት የሚሰራ ግብር-ኃይል መቋቋሙን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.