Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የቤት ኪራይ ዋጋ እንዳይጨመር የተደረገው ክልከላ ለሶስት ወራት ባለበት ይጸናል

 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ቢሮ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተው ቀርቧል፡-

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የከተማችንን ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ሕብረተሰቡ በሚያደርገረው ከፍተኛ እገዛና ትብብር ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ ከባድ የጦር ሜዳ መሳሪያዎች ፤ ተቀጣጣይና ፈንጂ ቁሳቁሶች እነዲሁም የሽብር ተግባር ለመፈጸም በህቡ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከወቅታዊ የጸጥታ ስራዉ ባለፈ አዲስ አበባን በዘላቂነት አስተማማኝ የሰላም ከተማ የማድረግም ስራ እየተሰራ ነው፡፡

የጀመርነው ሁለንተናዊ ሰላም የማረጋገጥ ስራ ግቡን እንዲመታ ክፍተቶችን ፈጥነን እያረምን የጸጥታ ስራችንን ይበልጥ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡

በዚሁ መሰረት፡
1ኛ ጊዜያዊም ሆነ መደበኛ መታወቂያ መስጠት የተከለከለ መሆኑን ይመለከታል፡ የመታወቂያ አሰጣጥን በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 5/2014 መሰረት አንቀፅ 6(6) ላይ ለመታወቂያነት የሚያገለግሉ ሰነዶች የሌለው ሰው ጊዜያዊ የመታወቂያ ወረቀት የመያዝ ግዴታ እንዳለበት በተደነገገው መሰረት የጊዜያዊ መታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት መመሪያ ቁጥር 2/2014 ተግባራዊ ሆኖ ጊዜያዊ መታወቂያ ማግኘት የሚገባቸው ነዋሪዎች እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመታወቂያ አገልግሎት በየትኛዉም የግልም ሆነ የመንግስት መስሪያ ቤት እንዳይሰጥ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ክልከላ እያለ አንድ አንድ የጤና ተቋማት አዋጁን በሚጻረር መልኩ መታወቂያ እየሰጡ መሆኑን መንግስት ደርሶበታል፡፡
ይህ ተግባር ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በቀጥታ የሚቃረን እና ሰላም የማስከበር ስራችን ላይ እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅት የትኛዉንም አይነት መታወቂያ እንዳይሰጥ እጥብቀን እናሳስባለን ፡፡

ይህን አዋጅ ተላልፎ በሚገኝ የትኛዉም አካል ላይ የከተማው አስተዳደር አስፈላጊውን ህጋዊ ጥብቅ እርምጃ የሚወስድም ይሆናል፡፡
በተለይም ደግሞ ክቡር የሆነውን የህክምና ሙያን ሽፋን በማድረግ መታወቂያ እየተሰጠ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ እንዲህ አይነት ኃላፊነት የጎደለውን ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ ክትትል በማድረግ መንግስት አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል፡፡

የከተማችን ነዋሪዎች ሕገወጦችንና ጸጉረ ልዉጦችን በማጋለጥ እና አሳልፎ በመስጠት፤ ለከተማዉ ሰላምና ጸጥታ ደጀን በመሆን ረገድ የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪችንን እናቀርባለን፡፡

2ኛ. የቤት ኪራይን ይመለከታል፡ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የመዲናችንን ነዋሪ የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከተከራየበት ቤት ማስለቀቅ እንደማይቻል ውሳኔ ማተላለፉ ይታወሳል፡፡

ይህ ያለንበት ወቅት አገርን ከተጋረጠባት የህልዉና አደጋ የማዳን በመሆኑ ውሳኔውን ለቀጣይ ሶስት ወራት ባለበት እንዲጸና ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በመሆኑም ከሕዳር 17 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣይ ሶስት ወራት የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ማስለቀቅ ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.