Fana: At a Speed of Life!

በመጭው ሃገራዊ ምርጫ የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት?

አዲስ አበባ ፣ ጥር 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ምሁራን በገለልተኝነት ሚዛናዊ የሆኑና ለሀገር የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ማቅረብ ላይ ሊሳተፉ እንደሚገባ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የተለያዩ ዘርፍ ምሁራን ተናገሩ፡፡

ከስሜት በፀዳ እና በእውቀት የተመራ የሀሳብ ሙግቶች ላይ በመሳተፍ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት መስራት አለባቸውም ብለዋል።

የአስተዳደርና የልማት ጥናት ተመራማሪው ዶክተር ራስፍው ኢንጂፈቶ መጭው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሀገሪቱ ምሁራን ሚናቸው ጉልህ መሆኑን አስረድተዋል።

ተራርቀዋል ለሚባሉት ፅንፍ የወጡ ጉዞዎች ወደ ሀገራዊ መግባባትና ሁሉን አሳታፊ ወደ ሆነው ምህዳር ማምጣት የፖለቲካ ሀይሉንም ሆነ ህዝቡን በእውቀትና እውነት የመግራት ሀላፊነትን ምሁራኑ እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ዳዊት ሀይሶ፥ ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ብቁ የሆኑ ምሁራን ማፍራቷን ያነሳሉ።

ይሁን እንጅ እንደ ምሁር መንቀሳቀስ እና ጠንካራ ሀሳቦችን የማቅረብ ተግባርን መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በምርጫው ሂደት ለሀገሪቱ የሚጠቅመው ሀሳብ ላይ ብቻ መከራከር የምሁራኑ ዋነኛ ትኩረት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

ሊገጥሙ በሚችሉ ፈተናዎችም የመፍትሄ አማራጮችን እስከ ማቅረብ የሚደርስ ርቀት መሄድ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሚዛናዊ የሆኑ ሀሳቦችን ለማንሸራሸር ደግሞ ምሁራኑ ገለልተኛ ሆነው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ምሁራኑ በአመታት የጥናት እና ምርምር ድግግሞሽ ውስጥ ያገኟቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች በምርጫ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ስጋቶችን ለመፍታት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግጭት አፈታት እና አስተዳደር ላይ የምርምር ስራዎችን የሚሰሩት ዶክተር ሙሉጌታ ዱካሎ በበኩላቸው፥ ምሁራን የህዝቡን ፍላጎት መሰረት አድርገው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ መርምሮ የሚበጀውን አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ እንዳለባቸው ይገልጻሉ።

እንዲሁም ለየትኛውም ቡድን ሳይወግኑ ለሙያቸው እና ለህዝባቸው ተገዢ መሆን እንዳለባቸውም ጠቅሰው፥ አሁን ላይ ከምሁራን የሚቀርቡ ሀሳቦችን ለመቀበል ከመንግስት ተነሳሸነት መኖሩን አንስተዋል።

ምሁራኑ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰጣቸውን ክብርና ተደማጭነት ለሀገር የሚበጀውን ምልከታ ግልጽ አድርገው መተንተን ላይ እንዲሳተፉም ጠይቀዋል።

በአጠቃላይ ምሁራኑ በምርጫው ሂደት በገለልተኝነት ለሀገር በሚበጁ እና የነገውን ተስፋ በሚጠቁሙ ሀሳቦች ላይ ቢያተኩሩ መልካም መሆኑን አውስተዋል።

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.