Fana: At a Speed of Life!

በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴው ግድብ 40 ሺህ ዶላር አበረከቱ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ያሰባሰበውን የ40 ሺህ ዶላር ድጋፍ አስረከበ፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ ቄስ ፍራንሲስ ኮሚቴው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚነዙ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለመመከትና ለግድቡ ግንባታ የሚሆን ሃብት ለማሰባሰብ መመስረቱን ገልጸዋል፡፡

ኮሚቴው ሁለተኛ 40 ሺህ ዶላር እያሰባሰበ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃብት ከማሰባሰብ ጎን ለጎን ከልዩ ልዩ አካላት ጋር በመተባባርና የአሜሪካ ምክር ቤት ተመራጮችን በማግባባት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሚኔሶታ የኢፌዴሪ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር አብዱላዚዝ መሐመድ በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ከፍተኛ ሃብት በማሰባሰብ የሃገር ባለውለታነታቸውን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአካባቢው የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በዚህ ሳይወሰኑ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና በሃገር ውስጥ የቀጥታ ኢንቨስትመንት እያሳዩት ያለው ተሳትፎም የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዳያስፖራው እያደረገ ላለው አበረታች እንቅስቃሴ አመስግነው፥ ዳያስፖራው ከጊዜያዊ ልዩነት ይልቅ ለሃገራዊ አንድነት እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ዳያስፖራው፥ በኮቪድ19 ምክንያት ችግር ውስጥ ሆኖ ሃገሩን ለማገዝ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም ወቅቱ ዳያስፖራው ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን አጠናክሮ ለሃገሩ የሚቆምበት ወቅት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.