Fana: At a Speed of Life!

በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ተመደበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላው አገሪቱ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መመደቡን የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ከካፒታል ዕቃ ፋይናንስና ከስራ ማስኬጃ ብድር አቅርቦት የስራ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በሚታዩ ወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ ከክልሎች እና ከፌዴራል የፋይናንስ ተቋማት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የፌደራል፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበራትና ሌሎችም በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንደገለጹት÷ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይም የማሽን አቅርቦት፣ የስራ ማስኬጃ ብድር አቅርቦት እና ለፕሮጀክት ፋይናንስ የሚሆን የድጋፍ ችግሮችን በመፍታት ኢንተርፕራይዞቹን ለመደገፍና ዘርፉን ለማጠናከር 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መመደቡንም ነው የገለጹት።

ገንዘቡ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ለሁሉም ክልሎችና ለሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የሚሰራጭ መሆኑን ገልጸዋል።

የማሽነሪና የብድር አቅርቦቱን በማሻሻል እንዲሁም ፕሮጀክቶች ለመደገፍ የሚያግዝ ፋይናንስ ለተቋማት ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ የሚመቻች መሆኑንም ነው የገለጹት።

በዚህም ጥሬ እቃና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርቡ የአገር ውስጥ አምራቾች የሚሳተፉ ናቸው ተብሏል።

በቀጣይም በከተሞችና ወረዳዎች ላይ ኢንዱስትሪዎችን የማቋቋም ስራ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ የተለያዩ የካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበራት ከፋይናንስ አቅርቦቱ ባሻገር የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ፣ የመሰረተ ልማት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም ጥራት ያላቸውን ማሽነሪዎች የማቅረብ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የካፒታል እቃ አቅርቦቱን ማሻሻል የዋስትና፣ የቴክኖሎጂ፣ የማሽነሪ አቅርቦት ችግሩን በመፍታት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።

በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላቶች በቅንጅት በመስራት ኢንተርፕራይዞቹ የገበያ ትስስር እንዲያገኙና ምርታቸውን በቀላሉ የሚሸጡበት ሁኔታ እንዲመቻች መስራት ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.