Fana: At a Speed of Life!

በማዕድን ዘርፍ በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ 500 የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ መታቀዱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ 500 የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና 1 ሺህ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ማቀዱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማትና ከክልሎች ጋር የልማት ዕቅዶች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ፣ ከኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽንና ከክልል ማዕድን ኃላፊዎች ጋር የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ፣ የ2013 በጀት አመት እቅድና የአንደኛ የሩብ አመት አፈጻጸም ዙሪያ በአዳማ ከተማ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱም በዘርፉ በሚቀጥሉት 10 አመታት ውስጥ 500 የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና 1 ሺህ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መታቀዱ ተነስቷል።

እንዲሁም በኩባንያዎች 127 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ በባህላዊና በኢንተርፕራይዞች ደግሞ 10 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት እቅድ መያዙም ተነስቷል።

በተጨማሪም ኩባንያዎች 100 ሺህ በሜትር ኪዩብ የእምነበረድ ማዕድን ይመረታል መባሉንም ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል በባህላዊና በኢንተርፕራይዞች 30 ሺህ 20 ነጥብ 8 ቶን የኢንዱስትሪ ማዕድናትና 30 ሺህ 000 ኪሎ ግራም የጌጣጌጥ ማዕድናት የሚመረት ይሆናል፡፡

በ2013 ዓ.ም አንደኛ ሩብ አመት የተለያዩ ማዕድናትን በማምረትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 178 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱም ተነስቷል።

በውይይቱ ላይ በዘርፉ ያሉ ችግሮች የተነሱ ሲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ህገወጥነትን በመከላከል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል።

ክልሎችም ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት በመስጠት ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠርና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቅሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.