Fana: At a Speed of Life!

በምሥራቅና በምዕራብ የተገኘው ድል በመሐል ሀገር እንደሚደገም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጡ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምሥራቅና በምዕራብ የተገኘው ድል በመሐል ሀገር እንደሚደገም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄንን የተናገሩት በሦስተኛው ቁልፍ ግንባር ተገኝተው ከሠራዊቱ ጋር በመከሩበት ጊዜ ነው።

ከሰሞኑ በሚሠሩ ኦፕሬሽኖች በወራሪው አሸባሪ የተያዙ ተጨማሪ ከተሞች ነጻ እንደሚወጡ የገለጡ ሲሆን ለወረራ የገባው አሸባሪ ምንም ነገር ይዞ እንዳይወጣ ሕዝቡ ተደራጅቶ ማስቀረት እንዳለበት ጥሪ አድርገዋል።

ጠላት ፈርሷል፤ ተበትኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አሁን ጠላት ያለው አማራጭ የሰረቀውን አስረክቦ እጁን መስጠት ነው ብለዋል።

የሰረቀውን አስረክቦ እጁን ከሰጠ ምርኮኞችን ተከባክቦ መያዝ የጀግና ባህላችን ነው ብለዋል።

ከአሸባሪው ሕወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች በአስቸኳይ መስተዳድሩን በቶሎ መልሶ ማቋቋም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነዋል። ወታደሩ በከፍተኛ ሞራል ላይ ነው ሲሉም የወገን ኃይል ያለበትን ገልጠዋል።

ሕዝቡ እስካሁን ላደረገው ተሳትፎ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን አንድነታችን የተጠበቀ ይሁን፤ የአሉባልታ ወሬ ወጀብ አይውሰደን፤ አንድ ሆነን የማትደፈር ሀገር ለልጆቻችን እናስረክብ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልእክት አስተላልፈዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.