Fana: At a Speed of Life!

በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው ከ18 እና 20 ዓመት በታች ልዑክ አቀባበል ተደረገ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ4ኛ ጊዜ በዳሬሰላም በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ለተሳተፈው ልዑክ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ÷ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራን ጨምሮ ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮች እና የማናጅመንት አባላት በአበባ ጉንጉን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ÷ ቡድኑ በቆይታው የምግብ፣ የትራንስፖርትና የማረፊያ ችግር ገጥሞት እንደነበር አስታውሰው ሁሉንም ችግር በኢትዮጵያዊ ወኔ በማለፍ ለድል በመብቃቱ ይደነቃል ብለዋል፡፡

አትሌት ገዛኸኝ አበራ በበኩላቸው÷ የተገኘው ውጤት ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው ሻምፒዮናው ለነገው አትሌቲክሳችን ተስፋ ሰጪ ነው ማለታቸውን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር መስፍን ቸርነት ድሉ ከመቼውም በላይ አነቃቂና ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ የነገ ተተኪወቿን እናንተን ስለምትጠብቅ ጠንክራችሁ ስሩ ብለዋል፡፡

አትሌቶች ባስመዘገቡት ውጤት መሠረትም የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በስምንት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ሲካሄድ በቆየው ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች የታዳጊ አትሌቶች ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ17 ወርቆች፣ በ3 ብሮች፣ በ2 ነሃሶች፣ እና በ2 ዲፕሎማዎች በከፍተኛ የሜዳልያ ብዛትና ልዩነት በመያዝ በቀዳሚነት ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.