Fana: At a Speed of Life!

በምርጫው ዕለት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ለማድረግ ባለሙያዎችን አሰማርቻለሁ – ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በምርጫው ዕለት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ለማድረግ ባለሙያዎችን ማሰማራቱን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጁ አንቀፅ 6 መሰረት በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅን ክትትል የማድረግ ስልጣን እና ሀላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

በዚህም ነገ በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ ለመከታተል የምርጫ ክትትል ቡድኖች በማቋቋም ምርጫ በሚካሄድባቸው በሁሉም ክልሎች ባለሙያዎችን አሰማርቷል፡፡

የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ምርጫ ክትትል ቡድኖች በሚሰማሩባቸው ስፍራዎች በምርጫው ዕለት እና ከምርጫው በኋላ ባሉት ቀናት በምርጫ ጣቢያዎችም በመገኘት ምልከታ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መራጮችን፣ የምርጫ አስተባባሪዎችን፣ የፀጥታ አካላትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ እጩዎችን፣ ታዛቢዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር መረጃዎችን እንደሚያሰባስቡ እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያዎች እና በሕክምና ተቋማት በመገኘትም አስፈላጊውን ክትትል ያደረጋሉም ነው የተባለው፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በምርጫው ወቅት ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀላፊነት መሆኑን አስታውሰው፥ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ በግልፅ በተቀመጠው መሰረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት ትብብር የማድረግ ግዴታቸውን እንዲወጡ እና በክትትል ስራ ለሚሰማሩት የኮሚሽኑ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማንኛውም ሰው እና ተቋማት በሙሉ የኮሚሽኑን መለያ ካርድ (ባጅ) በመያዝ ለሚሰማሩት የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ምርጫ ክትትል ቡድን አባላት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ማንኛውም ሰው ለክትትል ቡድኑ አባላት ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ መረጃ እና ጥቆማ ማቅረብ የሚችል ሲሆን፥ በኮሚሽኑ የነፃ የስልክ መስመር 7307 ላይ በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚችል ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.