Fana: At a Speed of Life!

በጉጂ ዞን የሚንቀሳቀሱ የሸኔ ታጣቂዎች ከቡድኑ በመውጣት ለጸጥታ አካላት እጃቸውን እየሰጡ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጉጂ ዞን የሚንቀሳቀሱ የሸኔ ታጣቂዎች ከቡድኑ አፈንግጠው በመውጣት ለጸጥታ አካላት እጃቸውን እየሰጡ መሆኑን የአይን እማኞች ገለፁ።

መንግሥት የሸኔ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ እያደረገ ያለውን ጥረት ተከትሎ በርካታ የቡድኑ አባላት ለጸጥታ አካላት እጃቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

ለአብነትም ሰሞኑን ብቻ በርካታ የሸኔ አባላት እጃቸውን ለመንግሥት የጸጥታ አካላት ሰጥተዋል፡፡

ለጉዳይ ቅርበት ያላቸው የአይን እማኞች በጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ አካባቢ በመንቀሳቀስ ላይ ካሉት የቡድኑ ታጣቂዎች መካከል  መሀመድ ሁሴን (ፈልማታ)፣ ጣይር አብዱሮ(ድዳ) እና ቱሳ አቡ(ለሚ) ለመንግስት እጃቸውን ሰጥተዋል።

የቡድኑን አባላት ፎቶዎች አያይዘው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላኩት መረጃ ላይ እንዳመለከቱት፥ ሶስቱን የቡድኑን ታጣቂዎች ጨምሮ በርካታ አባላት በሰላማዊ መንገድ በነገሌ ቦረና ለሚገኙ የኦሮሚያ ፖሊስና ሚሊሻ እጅ ሰተጥተዋል፡፡

ሌሎች ታጣቂዎችም አመቺ ሁኔታ እየጠበቁ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው የገለፁት የአይን እማኞች፥ ለበርካታ የሸኔ ታጣቂዎች ቡድኑን መክዳትና ሰላማዊ ህይወትን ምርጫ ማድረግ ምክንያቱ ውስጣዊ መከፋፈሉና ልዩነቶች ከግዜ ወደ ጊዜ እየጠነከሩና እየሰፉ መምጣታቸው እንዲሁም ምግብን ጨምሮ የሌሎች ግብዓቶች እጥረት እና ጫካ ለጫካ ያለምንም ግልፅ ዓላማ መንከራተት የነፍጥ ትግሉን አሰልቺ እና አስቸጋሪ ስላደረገባቸው መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አረጋግጠዋል፡፡

በቡድኑ ታጣቂዎች መካከል ለተፈጠረው ልዩነት ዋነኛው ምክንያት ከነፍጥ ይልቅ ልዩነታችንን በውይይትና በድርድር እንፍታ የሚለው አንጃ ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱ መሆኑ ተመልክቷል።

ይህን ተከትሎ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሸኔ ታጣቂዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ከቡድኑ አምልጠውና አፍንግጠው እየወጡ ለመንግስት እጃቸውን ለመስጠት አመቺ ሁኔታዎችን እየጠበቁ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.