Fana: At a Speed of Life!

በምግብ ራሷን የቻለች አገር ለመፍጠር በተፋሰስ ልማትና ጥበቃ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው – ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራሷን የቻለች አገር ለመፍጠር በተፋሰስ ልማትና ጥበቃ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአገር አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው የበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ በወቅቱ እንደገለፁት÷ የተፈጥሮ ሀብት ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለአገራዊ ሉዓላዊነት መረጋገጥ የላቀ ሚና አለው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የአፈር መሸርሸር፣ የአፈር አሲዳማነት መጨመር፣ የደን ምንጣሮ፣ የግጦሽ መስፋፋትና ህገወጥ ሰፈራ “ለተፈጥሮ ሀብት መመናመን ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
“በዚህም አገራችን የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ ተስኗት ለተመፅዋችነትና ለውጭ እርዳታ ጥገኛ ሆናለች” ብለዋል።
“እርዳታ ሰጭ ሀገራት በድጋፍ ስም እጃችንን እየጠመዘዙ ፍላጎታቸውን ሊጭኑብን ይሻሉ” ያሉት ፕሮፌሰር ኢያሱ ሁኔታውን ለመቀልበስና ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር የተፋሰስ ልማት ላይ በትኩረት መስራት አለብን” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
የተፋሰስ ልማት ስራው ከጥር 2014 ዓ.ም መጀመሪያ እንደሚጀመር ያመላከቱት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ህዝቡ በህልውና ዘመቻው እያስመዘገበ ያለውን ድል በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዘርፍ መድገም እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
ለመጪው ክረምት የሚተከሉ ችግኞችን ማዘጋጀት፣ የአፈርና ውሃ ዕቀባ፣ ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ ደግሞ በተፋሰስ ልማትና ጥበቃ ስራ የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀን በሚቆየው የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.