Fana: At a Speed of Life!

በሩዋንዳ በቱትሲዎች ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ 27ኛ ዓመት መታሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሩዋንዳ በቱትሲዎች ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ 27ኛው ዓመት መታሰቢያ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

ስነ ስርዓቱ “ማስታወስ፣አንድነት እና መታደስ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ  ነው የተከበረው ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ባደረጉት ንግግር በፈረንጆቹ 1994  በሩዋንዳ በቱትሲዎች  ላይ በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን የሚሆኑ ቱትሲዎች በገዛ ዜጎቻቸው  ህይወታቸውን ማጣታቸውን ጠቅሰዋል።

በሩዋንዳ የተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል የመከፋፈል ፖሊሲና የጥላቻ ንግግር ውጤት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ የሠላም አስከባሪ ኃይል በመላክ፣ ለአደጋ ተጋላጮችን  በመጠበቅ  እንዲሁም በመልሶ ማቋቋም ሂደት የመሪነት ሚና መጫመቷን አምባሳደሯ አስታውሷል፡፡

በሩዋንዳ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል አስቀድሞ ማስቀረት የሚቻል መሆኑን በኢትዮጵያ ሃሳብ አቅራቢነት የተቋቋመው አጣሪ ቡድን ማረጋገጡን በማስታወስ፤ ተመሳሳይ ወንጀሎች በየትም ቦታ እንዳይፈጸሙ  ኢትዮጵያ  ከህብረቱ አባል ሀገራት፣ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል።

ሩዋንዳ ከዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በኋላ ሀገር በቀል የዳኝነት ስርዓት በማቋቋም ወደ እርቅና ሀገር ግንባታ የገባችበትን ሂደት የሚያስመሰግናት መሆኑንም መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታሉ፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ፣ የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር  ዶ/ር ሞኒከ ኒሳንዛባጋነዋ ፣ የተ.መ.ድ ልዩ ተጠሪና በአፍሪካ ህብረት የተ.መ.ድ ቢሮ ኃላፊ ሃና ቴተህ ፣ በኢትዮጵ የሩዋንዳ አምባሳደር ሆፕ ቱሙኩንደ ጋሰታራ ፣ አምባሳደሮች እና የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።

የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ መታሰቢያ ፕሮግራም ዓላማው የአፍሪካ አባል ሀገራት እና ሌሎች አጋር አካላት የጥላቻን አስተሳሰብ፣ የዘር ማጥፋት እና የጥላቻ ወንጀሎች በጋራ ለመከላከል እንዲሁም ሩዋንዳ ከዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በኋላ ወደ እርቅና ሀገር ግንባታ የገባችበትን ሂደት ልምድ ለማካፈል እንዲሁም ተመሳሳይ ድርጊት በአፍሪካ አህጉር እንዳይከሰት ለመከላከል  ነው፡፡

የአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ለመከላከል እና ቁርጠኝነቱን ለማሳየት በየዓመቱ መጋቢት 29 እንዲታሰብ  ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.