Fana: At a Speed of Life!

በሰሜኑ ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ እየተደረገ ያለውን ምርመራና ድጋፍ በተመለከተ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ማብራሪያ እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ እየተደረገ ያለውን ምርመራ እና የድጋፍ ስራ አስመልክቶ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ማብራሪያ እየሰጠ ነው።
የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጽሕፈት ቤት ሰብሳቢ የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በሰጡት ማብራሪያ፥ በሀገራችን የሰሜኑ ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ በአፋርና በአማራ ክልሎች ከተፈጸመው ወንጀሎች ጋር በተያያዘ እየተከናወነ ያለው ምርመራ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ሁሉ አቀፍ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ እየተካሄደ ነው መሆኑን አንስተዋል፡፡
የግብረ ኃይሉ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ታደሰ ካሳ፥ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችን እና ጥናቱ የደረሰበትን ደረጃ አቅርበዋል።
መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በዜጎች ላይ የደረሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጥምረት ባካሄዱት የምርመራ ውጤት ሪፖርት ላይ የተመላከቱ ምክረ ሀሳቦችን በጥልቀት አይቶ ምላሽ ለመስጠት የሚኒስትሮች ግብረ-ሃይል በማቋቋም እንዲሁም የተጠቃለለ ስትራቴጂ እና ዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱ ይታወሳል።
ግብረ ኃይሉ በዋናነት በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕት ቤት እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥምር የምርመራ ቡድን ግኝትና ምክረ ሀሳብ ላይ በመመስረት በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የመመርመርና አጥፊዎችን ተጠያቂ የማድረግ እንዲሁም ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ኃላፊነት ተሰጥቶትና አራት ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
በሀብታሙ ተ/ስላሴ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.