Fana: At a Speed of Life!

በሰብዓዊ መብት ሰበብ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ ይገባል ሲሉ ቻይናና ሩሲያን ጨምሮ 13 ሀገራት ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣መስከረም 11 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ ዘንድ ሁሉም ተዋናዮች ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ያለምንም አድልዎ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ሲሉ ቻይናና ሩሲያን ጨምሮ 13 ሀገራት ጥሪ አቀረቡ።
በተጨማሪም ሰብዓዊ መብቶችን እንደሰበብ በመጠቀም በሉዓላዊ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ ይገባል ሲሉም  ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፍትሃዊነትና እኩልነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰፍን የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመባቸውን ዓለም አቀፍ መርሆዎች መሰረት ያደረገ ፍትሃዊነትና እኩልነትን በማረጋገጥ የተናጠል እንቅስቃሴዎችን መታገል ይገባልም ነው ያሉት።
አስራ ሶስቱን ሀገራት በመወከል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ቼን ሹ ባስተላለፉት መልእክት፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብቶችን በመጠበቅ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት መሰረታዊ ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሰብአዊ መብቶች መከበርን ለማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፋዊ ስርዓቱን እውነተኛ እና ፍትሃዊ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ይህንን እውን ለማድረግም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብርን ከማጠናከርም ባለፈ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ አንስተዋል።
በተጨማሪም ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት በጋራ ጥረት የዓለምን ደህንነት ማረጋገጥ እና የጋራ ብልፅግናን እውን ማድረግ ይቻላልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ፥ ሰላም፣ እኩልነትና ፍትህ እንዲሰፍን እንዲሁም ዴሞክራሲና ነፃነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማረጋገጥ ሁሉም የድርጅቱ አባል ሀገራት በአንድነት እንዲሰሩም ጥሪ ማቅረባቸውን ከሲጂቲኤን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.