Fana: At a Speed of Life!

በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ የሚደግፍ ሰልፍ አካሄዱ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን “ለሀገራችን  ሉዓላዊነትና አንድነት ከመንግስታችን ጎን እንቆማለን” በሚል መሪ ቃል ህዝባዊ የድጋፍ  ሰልፍ አደረጉ።

በሺዎች የሚቆጠሩ በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን  መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ በመደገፍ እና በአንዳንድ የውጭ አካላት የሚደረገውን ያልተገባ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመቃወም ነው  ሰልፉን ያካሄዱት፡፡

በካርቱም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማዕከል በተካሄደው በዚህ ደማቅ ሰልፍ የሐይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ሴቶች እና ወጣቶች መሳተፋቸው ተገልጿል።

ሰልፈኞቹ  በፕሮግራሙ ማብቂያ ባወጡት ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫም ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን  አጸያፊ ጥቃት እና የሀገር ክህደት ወንጀል አውግዘዋል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎ መንግስት የወሰደው አፋጣኝ ህግ የማስከበር እርምጃ ሀገርን ከመበተን የታደገ መሆኑን ገልጸዋል ።

ሰልፈኞቹ በአንዳንድ የህወሓት ርዝራዦች እና ደጋፊዎች እየተካሄደ ያለውን የሐሰት መረጃ ስርጭት እና ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም በአንዳንድ ሀገራት እና ድርጅቶች እየተሞከረ ያለውን ጫናንም አውግዘዋል።

መንግስት ከህግ ማስከበሩ ጎን ለጎን በክልሉ በህወሓት የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የወሰደውን እርምጃ እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ንጹሐን ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የወሰደውን እርምጃም አድንቀዋል።

በሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ  ÷ ኢትዮጵያውያኑ ለሀገራቸው አንድነት  ከመንግስታቸው ጎን በመቆም ያደረጉትን ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ አድንቀዋል።

ህወሃት ለውጡን ተከትሎ የበላይነቱን በማጣቱ ብቻ ሀገርን ለመበተን ክህደት መፈጸሙንም ገልፀዋል።

ቡድኑ ከአነሳሱ ጀምሮ አገራዊ ራእይ የሌለው ጠባብ ቡድን መሆኑን አምባሳደሩ  ጠቅሰው÷ ተሳክቶለት ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ እና በቀጠናው ሊፈጠር ይችል የነበረውን አደጋ እጅግ የከፋ ይሆን ነበር ብለዋል።

ሆኖም በመንግስት ብልሃትና በሰራዊቱ ጥንካሬ በአጭር ጊዜ ሴራው ሊከሽፍ እንደቻለ ገልጸዋል።

ህግ የማስከበሩን ተግባር በብቃት ብንወጣም የህወሓት ርዝራዦች፣ ተከፋዮቻቸው እና አንዳንድ አካላት በቡድኑ ላይ ነፍስ ለመዝራት በአገራችን ላይ ያልተገባ ጫና በማድረግ ላይ ይገኛሉም ነው ያሉት።

በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ዘብ መቆም እንደሚገባውና በመገናኛ ብዙሀን የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎችን እና ፕሮፖጋንዳ ለማክሸፍ ተግቶ እንዲሰራ መጠየቃቸውን ሱዳን ከሚገኘው  የኢትዮጵያ ኤምባሲ  ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.