Fana: At a Speed of Life!

በሲሚንቶ ምርትና ግብይት ላይ የታየውን የገበያ አለመረጋጋት ለመቅረፍ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሲሚንቶ ምርትና ግብይት ላይ የታየውን የገበያ አለመረጋጋት ለመቅረፍ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከክልልና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሲሚንቶ አምራቾችና አካፋፋዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት የሲሚንቶ አቅርቦትና ስርጭት ችግር ለመፍታት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኮሚቴ ተዋቅሮ ለፋብሪካዎች የማምረት አቅም ማነስ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን የመለየት ስራ በማከናወን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተለይም የሲሚንቶ ማከፋፈልን በተመለከተ የፋብሪካዎችን ወቅታዊ የማምረት ዓቅም መሰረት በማድረግ ጊዜያዊ ችግሮችን ለመፍታት በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት አምስት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ስርጭት እንዲገቡ በማድረግ እንዲሁም በፋብሪካዎች የተመረጡ የግል አከፋፋዮችን ህጋዊነትና የቀድሞ መረጃዎች በማጣራት ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በእኩል ምርቶችን እየገዙ ለህብረተሰቡ እንዲያከፋፍሉ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በየዕለቱ ከፋብሪካዎች ተመርተው የወጡ ምርቶችን ስርጭት በመከታተል የተከናወኑ ተግባራትን፣ ያጋጠሙ ችግሮችን የተጠቃለለ የሪፖርት ግንኙነት በመዘርጋት አፈፃፀሙን በትኩረት የመከታተል፣ የመደገፍና የመምራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዋናነት ከምርት እስከ ስርጭት ያለውን የሲሚንቶ የግብይት ስርዓት በመዘርጋት ምንም እሴት ሳይጨምሩ ኩፖን ብቻ በመሸጥ በሲሚንቶ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ሲያደርጉ የነበሩ ህገ-ወጥ ደላሎች እንዲወገዱ በማድረግ የችርቻሮ ዋጋ በአንፃራዊነት ወደነበረበት እንዲመለስ የማድረግ ስራ መሰራቱን አቶ መላኩ ማስረዳታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በቀጣይ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም የሚገድቡ ተግባራትን በጥብቅ ክትትል በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና በአካባቢያቸው የኢንዱስትሪ ሰላምና ጸጥታን ማስጠበቅ እንዲሁም ህጋዊ አከፋፋዮችን በመከታተል ከህጋዊ የስርጭት መስመር እና ወቅታዊ የሽያጭ ዋጋ በላይ በሚሸጡ ማናቸውም አከፋፋዮች እና ቸርቻሪ ነጋዴዎች ላይ ንግድ ፈቃድ ማገድና መሰረዝ፣ እንዲሁም በህግ ተጠያቂ የማድረግ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አስገንዝበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.