Fana: At a Speed of Life!

በሲዳማና ኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች ዘላቂ ሠላምና ልማትን ለማጠናከር የሚያግዝ የጋራ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ ዘላቂ ሠላምና ልማትን ለማጠናከር የሚያግዝ የጋራ ምክክር መድረክ በቦንሣ- ዳዬ ከተማ ተካሄደ።

ከትላንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ ከሁለቱ ክልሎች የተወጣጡ የሥራ ሃላፊዎችና ተወካዮች፣ የ11 አጎራባች ወረዳዎች የአስተዳደር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በሲዳማ ክልል የኦኮ ወረዳ ሠላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ጠንጠላ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል ሁለቱ ተጎራባች ህዝቦችን ሲያጋጩ ነበሩ ተብለው ከተለዩ ችግሮች ውስጥ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴና የቤት እንስሳት ዘረፋ ዋነኞቹ ናቸው።

ከለውጡ ወዲህ ግን የተቀናጀ አሰራር ተዘርግቶ የህብረተሰቡ ተወካዮች ለሠላምና ለአብሮነት ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ችግሮቹ እየተቃለሉና የእርስ በእርስ ግንኙነቱም እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አማኑኤል መንግሥቱ በሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት ሲፈቱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከርና ሠላሙ ዘላቂ እንዲሆን ለማስቻል ታስቦ የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

” አሁንም ያልተሻገርናቸው እንደ ኮንትሮባንድ ያሉ ለግጭት በሚዳርጉ ጉዳዮችና ህብረተሰቡን በሚያስተሳስሩ ልማቶች ዙሪያ በመምከርና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ በቀጣይ ርብርብ ለማድረግ ጭምር መድረኩ ተዘጋጅቷል” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ጉጂ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ መምሪያ ኃላፊ አቶ ወልዴ ኡጎ እንዳሉት፤ የለውጡ አመራር የሁለቱን አጎራባች አካባቢዎች ህዝቦችን ወንድማማችነት ለማጠናከርና ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን እያካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.