Fana: At a Speed of Life!

በስራ ላይ ያለውን ስርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በስራ ላይ ያለውን ስርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በአዲስ ስርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በስራ ላይ ያለውን ስርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የአስር ዓመታት ፍኖተ-ካርታ መዘጋጀቱን በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው በጉዳዩ ዙሪያ በተዘጃጀ የባለሙያዎች ምክክር መድረክ ላይ ተናግረዋል።

በመጭዎቹ ዓመታት በአዲስ የሚተካው ስርዓተ-ትምህርት የተማሪዎችን ስነ-ምግባር ጨምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቃዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ስርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ወርቁ በበኩላቸው ስርዓተ-ትምህርቱ እየተዘጋጀ ያለው ከፍኖተ ካርታው በተገኙ ምክረ ሃሳቦች መሆኑን ነው የተናገሩት።

እንዲሁም የካንብሪጅ ኢንተርናሽናል ግምገማን ጨምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻዎች በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ተጨማሪ አስተያየት መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ በተዘጃጀ የባለሙያዎች ምክክር መድረክ ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች፣ የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ሃላፊዎች፣ ከሁለተኛና ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራን፣ የመምህራን ኮሌጆችና ከአምስቱ የመምህራን ማሰልጠኛ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.