Fana: At a Speed of Life!

በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለማቋቋም በቂ ዝግጅት እንዲደረግ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በቂ ዝግጅት እንዲደረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ለ20 ሚሊየን ተረጂዎች የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው ብሏል።

የኮሚሽኑ የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃጸምን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በጅግጅጋ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በርካታ ዜጎች ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን ጠቅሰው፥ የምላሽ አሰጣጥ ሂደቱ ካጋጠመው ችግር ጋር ሲነፃፀር  በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።

እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ምላሽ ለመስጠትም በዝርዝር በመገምገም በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው፥ በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተ የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ክልሉ በከፍተኛ የድርቅ አደጋ መመታቱን ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልልም በ9 ዞኖች ከፍተኛ የድርቅ አደጋ የተከሰተበት መሆኑን ጠቅሰው፥ በአደጋው 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች ተጎጂ ሲሆኑ፥ ከ2 ሚሊየን በላይ የቁም እንስሳትም መሞታቸውን አስታውሰዋል።

የድርቅ አደጋው ባጋጠማቸው አካባቢዎች የምግብ፣ የውሃ፣ የመድኃኒት እና የእንስሳት መኖ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በድጋፍ ሂደቱም የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ ረጂ ድርጅቶች፣ ሌሎች ተቋማትና ኢትዮጵያውያን ከክልሉ ህዝብ ጎን በመሆን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ÷ በድርቅና በጦርነት ለተጎዱ እንዲሁም ከሳዑዲ ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት 60 በመቶውን የተራድኦ ድርጅቶች ደግሞ 40 በመቶ በሚያደርጉት ድጋፍ ከ20 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ እንዲቀጥሉ ውይይት እየተደረገ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.