Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል በ372 ሚሊየን ብር በጀት አጣዳፊ የድርቅ ምላሽ ፕሮጀክት ስራ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በ372 ሚሊየን ብር በጀት አጣዳፊ የድርቅ ምላሽ ፕሮጀክት ስራ እየተካሄደ መሆኑን በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስታወቀ።
 
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙክታር መዓሊን አብዲ እንደገለጹ÷ ፕሮጀክቱ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ድርቁ ካስከተለባቸው ተፅዕኖ እንዲያገግሙ ከዓለም ባንክ በተመደበ በጀት ነው እየተካሄደ ያለው።
 
የግጦሽ መሬትን ማስተዳደር፣ አርብቶ አደሩ ከድርቅና ከአየር ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም እንዲችል ማገዝ፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎች፣ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ተቋማት ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል በፕሮጀክቱ ትኩረት ከሚደረግባቸው መካከል ይገኙበታል።
 
አሁን ላይ 500 ሄክታር መሬት በፍጥነት የሚደርስ የተመጣጠነ የእንስሳት ሳር በጎዴ፣ በዶሎ አዶ፣ አዳድሌና ዶሎ ባይ ወረዳዎች ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመቀናጀት በመስኖ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።
 
እንዲሁም 11 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ 32 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች የማሻሻያና ጥገና ስራዎች እንዳሉም ጠቅሰው ÷ይህ ስራ የሚካሄደው ከውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር መሆኑን አስረድተዋል።
 
በጀቱ በክልሉ 54 ወረዳዎች የሚገኙ እንስሳትን ድርቁ ካስከተለው ጉዳት ለመታደግ በተለያዩ ተቋማት የተገዙ የእንስሳት መኖ የማጓጓዣ ወጪን እንደሚያካትትም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
 
ለ5 ዓመታት ለሚዘልቀው ፕሮጀክቱ ተጨማሪ በጀት እንዳለውና ከ2 ሚሊየን በላይ አርብቶ አደሮችን እና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.