Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል በሙስና በተጠረጠሩ 168 የመንግስት ሰራተኞች ላይ ክስ መሰረተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ፍትህ ቢሮ ሃላፊነትን ለግል ጥቅም በማዋልና በሙስና በተጠረጠሩ 168 የመንግስት ሰራተኞች ላይ ክስ መሰረተ፡፡
ክሱ በግብረአብረነት የተጠረጠሩ 17 ነጋዴዎችንም አካቷል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሃጂ እንደገለጹት÷ በገቢ ማሰባሰብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ላይ በተደረገ የኦዲት ምርመራ 93 ሚሊየን ብር ጉድለት እንደተገኘ የሶማሌ ክልል ጠቃላይ ኦዲት ጽ/ቤት ለአቃቤ ህግ በላከው ሪፓርት ያረጋገጠ ሲሆን÷ይህን ተከትሎ በገንዘብ ምዝበራው ተሳትፎ አላቸው በሚል በተጠረጠሩ 168 የመንግስት ሠራተኞች ላይ ክስ ተመስርቷል፡፡
ቢሮው ከፖሊስ ጋር በመተባበር በወሰደው እርምጃም÷ እስካሁን ከተለያዩ ግለሰቦች 15 ሚሊየን ብር ተመላሸ ሆኖ ወደ መንግስት ካዝና መግባቱን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የሶማሌ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን÷ በሶማሌ ክልል ንግድና ትራንስፖርት ጽ/ቤት ሰራተኛ ሆነው የመንግስትና የህዝብ ሃብትን ለግል መጠቀሚያ በማድረግና በሙስና በተጠረጠሩ 14 ሠራተኞች ላይ ክስ የመሠረተ ሲሆን ከተከሳሾቹ መካከል ሁለቱ ዳይሬክተሮች መሆናቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።
ከነዚህ 14 ግለሰቦች መካከል 4ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ የቀጠለ ሲሆን÷ ቀሪዎቹን ለህግ ለማቅረብ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በግብረአብረነት ተሳትፎ እንዳላቸው በተጠረጠሩ 17 ነጋዴዎች ላይም ክስ መመስረቱን ተናግረዋል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ፣ አቃቤ ህግ እንዲሁም የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን÷ ከለውጡ በተለይም ከምርጫው በኋላ የተሰጣቸውን ህጋዊ ስልጣን እና ሃላፊነት እየተገበሩ እንደሚገኙ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
አሁን ላይ ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ ምርመራና ማጣራት በማካሄድ፣ መረጃዎችን በመቀበል፣በማጥናት እና በመተንተን ተጨባጭ የሆነ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ከህዝብ የደረሱ ጥቆማዎችን ተከትሎ በሌሎች የክልሉ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይም በተመሳሳይ መልኩ የምርመራ ሂደት በስፋት እየተከናወነ እንደሆነም ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ ሙስና፣ በስልጣን ያለ አግባብ መጠቀም እና በመንግስት እና በህዝብ ንብረት ላይ የሚፈፀሙ የአሰራር ብልሹነትን በመቃወም ጥቆማዎችን በመስጠት ላደረገው ብርቱ ትብብር አመስግነዋል፡፡
ሙስናን መፀየፍ እና ተፈፅሞም ሲመለከት በተመሳሳይ መልኩ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሶማሌ ክልል መንግሥት በሙስናና ብልሹ አሠራር ተዘፍቀው የሚገኙ ማንኛውም አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.