Fana: At a Speed of Life!

በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት የስራ ሃላፊዎች ላይ ፍርድ እና ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ጌታቸው አሰፋ ፣ ያሬድ ዘሪሁን እና ሌሎች 24 ተከሳሾች ላይ ፍርድ እና ብይን ተሰጠ ።

ተከሳሾቹ ከ1984 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያቤት በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች ተመድበው ሲሰሩ በህግ አግባብ የተሰጣቸውን ስልጣን መሰረት በማድረግ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ማለትም በአዲስ አበባ ባሉ ክፍለ ከተሞች፣ በአማራ ክልል ባህርዳርና ጎንደር፣ በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ፣ ጅማ፣ ሻሸመኔና ቢሾፍቱ፣ በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ ሰዎች የሚታሰሩበትን ሁኔታ በማመቻቸትና ድብቅ እስር ቤቶችና መመርመሪያ ክፍሎች እንዲዘጋጁ ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

በዚህም በማንኛውም ወንጀል የተጠረጠረን ሰው የመያዝ የማሰርና የመመርመር ስልጣን ሳይኖራቸው ከሽብር ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥራችኋል በማለት በሌሊትና በቀን ፣ ለወራትና ለአመታት ከታሰሩበት ድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ በላያቸው ላይ ውሃ እየደፉ በአፍ ውስጥ ካልሲ በመክተት ፣ የእግር ጥፍር በመንቀል፣ የተበዳዮችን የሰውነት ክፍል በኤሌክትሪክ በማስነዘር ፣ እጅና እግርን በብረት ሰንሰለት በማሰርና ጠረጴዛ ላይ በመስቀል ሚስማር ባለው ጣውላ እንዲደበደቡ ፣ በኤሌክትሪክና በሽቦ ገመድ እንዲገረፉ ፣ ራቁታቸውን ጉንዳን ውስጥ በማስገባት ፣ በብልታቸው ላይ ሃይላንድ በማንጠልጠል ፣ በአፍንጫቸው እስክርቢቶ በመስደድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ስልጣንን አላግባብ በመገልገል የሚፈፀም ከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸው የሚታወስ ነው ።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ እንደየተከሰሱበት አንቀፅ ጥፋተኝነታቸው በዐቃቤ ህግ ማስረጃዎች የተረጋገጠ በመሆኑ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አፅበሃ ግደይ ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሽሻይ ልኡል አራት ተከሳሾች በሌሉበት የጥፋተኝነት ፍርድም ተላልፎባቸዋል ።
የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁንና ሌሎች ተከሳሾች ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበው ብይኑንን የተከታተሉ ሲሆን ተከሳሾቹ አንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

ተከሳሾቹ በዋስ ወጥተን ክሳችንን እንከታተል ብለው ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም ዐቃቤ ህግ በዋስትና ጥያቄው ላይ በፅሁፍ አስተያየት ልስጥበት በማለቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለታህሳስ 6 ቀን 2014 ዓ.ም መሰጠቱን የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.