Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ አስር ቀናት በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ አስር ቀናት በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በዚህም በሚቀጥሉት አስር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዮሮሎጂ ገጽታዎች እየተጠናከሩ ሊሄዱ እንደሚችሉና በተለይም በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ሊኖር እንደሚችል ነው የተገለፀው፡፡

እንዲሁም ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በተጨማሪም የደቡብ፣ የመካከለኛውና የምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት ያገኛሉ ተብሏል፡፡

ይህም በክረምት ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ለሚጠበቀው የግብርና እንቅስቃሴ ጥሩ ጎን እንደሚኖረው እና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚጠበቀው እርጥበት፥ የአፈር ውስጥ እርጥበትን ከማሻሻል አንፃር አስቀድመው የተዘሩና በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግም ሆነ የረጅም ጊዜ የመኸር ሰብሎች እንዲሁም ለተለያዩ የቋሚ ተክሎችና የጓሮ አትክልቶች የውሀ ፍላጎታቸውን ከማሟላት አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው የተባለው።

በአንፃሩ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በተለይም ባሳለፍናቸው ቀናት በተከታታይ ዝናብ በማግኘት ላይ በሚገኙ ቦታዎች ላይ የአፈር ውስጥ እርጥበት መብዛት፣ እንዲሁም ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ከአፈር መሸርሸርም ሆነ ከመሬት መንሸራተት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኢኒስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም በልግ አብቃይ በነበሩት አካባቢዎች ላይ የሚጠበቀው ዝናብ የደረሱ የበልግ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በየጣልቃው የሚኖሩ ደረቅ ቀናትን በመጠቀም የሰብል ስብሰባ ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋልም ብሏል፡፡

በሌላ በኩል በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚጠበቀው እርጥበት በመጠን ዝቅተኛ ቢሆንም በተለይም ባሳለፍናቸው ቀናት አካባቢዎቹ ካገኙት እርጥበት ጋር ተዳምሮ የመጠጥ ውሀ አቅርቦትና የግጦሽ ሳር ልምላሜ ከማሻሻል አንጻር ጥሩ ጎን እንደሚኖረው መገለፁን ከኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢኒስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.