Fana: At a Speed of Life!

በቅዱስ ጳውሎስ የመካንነት ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ ጥንዶች ልጅ ማግኘት ችለዋል

አዲስ አበባ፣ጥር 5፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የመካንነት ሕክምና ማዕከል ህክምናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ጥንዶች በተደረገላቸው ህክምና ልጅ ማግኘታቸው ተገልጿል።

ለሰባት ዓመታት በጋብቻ ሲኖሩ ልጅ ማፍራት ያልቻሉት ጥንዶቹ ፥ ሆስፒታሉ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ባስጀመረው የመካንነት ሕክምና ማእከል በተደረገላቸው ክትትል ነው የመጀመሪያ ልጃቸውን ማቀፍ  የቻሉት።

ጥንዶቹ ልጅ ማግኘት የቻሉት የኢንትሮ ቪትሮ ፈርትላይዜሽን በተባለ ህክምና ሲሆን፥ በቀጣይ ወራቶች 70 የሚደርሱ እናቶችም በዚሁ ህክምና ልጃቸውን ያቅፋሉ ነው የተባለው።

በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት  የመካንነት  ችግር ስርጭት ከፍተኛ መሆኑ ቢታመንም በተወሰነ መልኩ ምርመራዎችን ከማድረግ የዘለለ በበቂ ሁኔታ የህክምና መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል የተደራጀ የህክምና ተቋም አልነበረም።

ለዚህ ህክምና በመንግስት የጤና ተቋም ደረጃ  የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የመጀመሪያው ነው።

ከዚህ ቀደም ብዙ ጥንዶች በከፍተኛ ወጪ  ለህክምናው ወደ ውጪሀገር ለመሄድ  ሲገደዱ፥ በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይባክን ነበር።

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ሆስቲታሉ በሀገር ውስጥ የማይገኙ ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችን ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑን ከሆስቲታሉ ያገኘነው  መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.