Fana: At a Speed of Life!

በቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ451 ሚሊየን ዶላር በጀት በስድስት ክልሎች በሚተገበር የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሚተገበረው የፕሮጀክቱ ልማት እቅዶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በጋምቤላ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ በሚኒስቴሩ የፕሮጀክቱ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ ዑመር እንደገለጹት የፕሮጀክቱ ዓላማ በክልሎቹ የህዝቡን ኑሮ ማሻሻል ነው።

ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከሚያደርጋቸው መካከል 50 በመቶ ሴቶች ሲሆኑ 20 በመቶዎቹ ደግሞ ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

“የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቱ የጋምቤላ ክልልን ጨምሮ በስድስት ክልሎች በሚገኙ 100 ወረዳዎች የሚተገበር ይሆናል” ብለዋል።

በስድስቱ ክልሎች ለተነደፉት የአምስት ዓመት የጤና፣ ትምህርት፣ መንገድ፣ ግብርናና ሌሎችም የልማት ዘርፎች ማስፈፀሚያ ከዓለም ባንክና ከግብርና ልማት ፈንድ የገንዘብ ተቋማት 451 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መመደቡንም አስታውቀዋል።

የጋምቤላ ክልል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ቤል ቢቾክ በበኩላቸው “በክልሉ ስምንት ወረዳዎች በቀጣይ አምስት ዓመት ከክልሉ ህዝብ 60 በመቶ የሚሆነውን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

የፕሮጀክቱ እቅዶች የማህበረሰቡን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ የታቀደ በመሆኑ ውጤታማ ይሆናል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.