Fana: At a Speed of Life!

በበይነ መረብ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አደገኛና ውስብስብ እየሆኑ መምጣታቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በበይነ መረብ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ይበልጥ ውስብስብ እና አደገኛ እየሆኑ መምጣታቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዋና ዋና የኮምፒውተር ሲስተሞችን የመጥለፍ ችሎታ ያላቸው መረጃ መዝባሪዎች አሁን ላይ የበይነ መረብ የደህንነት ስጋት መሆናቸውን በዘርፉ ላይ የወጣ አዲስ ሪፖርት አመላክቷል፡፡

ሪፖርቱ በፈረንጆቹ 2020 የበይነ መረብ ወንጀለኞችን በፍጥነት ለመለየት አስቸጋሪ ከመሆኑም ባለፈ የወንጀሉ ውስብስብነትም እየጨመረ መምጣቱን ነው ያመላከተው፡፡

በቅርብ አመታት ውስጥም በአሜሪካ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በርካታ መንግስታዊና የግል ድርጅቶች የመረጃ መዝባሪዎች ኢላማ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በዚህ ሳቢያም በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ኪሳራ ደርሷልም ነው ያለው ሪፖርቱ፡፡

ከዚህ ቀደም ግዙፍ መንግስታዊ ተቋማት ብቻ በወንጀለኞቹ ኢላማ ይደረጉ እንደነበር በሪፖርቱ የተጠቀሰ ሲሆን አሁን ላይ ግን ማንኛውም የቢዝነስም ሆነ መንግስታዊ ተቋም የዚህ ኢላማ ሆኗል ነው የተባለው፡፡

መረጃ መዝባሪዎቹ ጥቃቶችን ለማዘጋጀት በጣም ውጤታማ በመሆናቸው ዘራፊዎቹ ወደ ሲስተሙ ለመግባት እና ጥቃት ለመሰንዘር 45 ደቂቃ ብቻ እንደሚወስድባቸው የማይክሮሶፍት ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ማይክሮሶፍት በቅርቡ በመንግስት የሚደገፉ 16 የመረጃ መረብ መዝባሪዎችን መለየቱን ገልጿል፡፡

ኩባንያው ስለመረጃ መረብ መዝባሪዎቹ ማንነትና መገኛ ግን ያለው ነገር የለም፡፡

ምንጭ፡- ዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.