Fana: At a Speed of Life!

በበጀት ዓመቱ ሁለት ወራት ለሕዳሴው ግድብ ከ272 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7 ፣2013 ( ኤፍ.ቢ.ሲ)) በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ272 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ÷ዜጎች ለሕዳሴው ግድብ በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት ሐምሌና ነሀሴ ወራትም ከ272 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ገንዘቡ የተገኘው በቦንድ፣ በስጦታ እና በ8100 አጭር የጽሁፍ መልዕክት ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብሮች መሆኑንም ገልጸዋል።

ባለፈው ነሐሴ ወር ከ152 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ የግድቡ ግንባታ ሥራ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከፍተኛ ገንዘብ ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

በሐምሌ ወርም ከ119 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ገቢ መሰብሰቡን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ዲያስፖራው ባለፉት ሁለት ወራት ከ5 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.