Fana: At a Speed of Life!

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 80 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ተፈጸመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 80 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ መፈጸምን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን ገለጸ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጽዋየ ሙሉነህ ለመስሪያ ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት የሚውሉ የተለያየ ሞዴል ያላቸው761 ተሽከርካሪዎችና 1 ሺህ 369 ሞተር ሳይክሎች እንዲገዙ ጥያቄ ቀርቦ 330 ተሽከርካሪ ለመግዛት ጨረታ ወጥቶ ለአጽዳቂ ኮሚቴ መላኩን ጠቁመዋል።

ከዘጠኝ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የማዕቀፍ ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል የ102 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ውል የመዋዋል ሥራ እንደተከናወነም አመላክተዋል።

ውል ለፈረሙ አቅራቢዎች የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ ለማድረግ በብሔራዊ ባንክ በኩል በጀት መመደቡንም ነው የገለጹት።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተለያዩ ተቋማት የነበሩ 27 ተሽከርካሪዎች፣ 194 ያገለገሉ ንብረቶችና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች እንዲሁም 1 ሺህ 220 ኪሎ ግራም ቁርጥራጭ ብረቶች መወገዳቸውንም ተናግረዋል።

አገልግሎቱ በአሁኑ ወቅት በማዕቀፍ ስምምነት ለሦስት ዓመት የሚቆዩ 117 ውሎችን በእጁ ይዞ እያስተዳደረ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።

የተለያዩ የመንግስት ንብረቶችን በጨረታ በማስወገድ 10 ነጥብ 27 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.