Fana: At a Speed of Life!

በቡራዩ በሆቴል የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ተፈጥሮ በነበረ ግጭት በተወሰኑ ሰዎች ላይ መጠነኛ የአካል ጉዳት መድረሱን የከተማዋ አስተዳደር ገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቡራዩ በአንድ ሆቴል የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ በነበረ ግጭት በተወሰኑ ሰዎች ላይ መጠነኛ የአካል ጉዳት መድረሱን የከተማዋ አስተዳደር ገለፀ።

የከተማዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብደላ ጢቤሶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንድገለፁት፥ ትናንት በከተማዋ የአንድ ሆቴል ምረቃት ላይ የነበረው ግጭት መንስኤ በስነ ስርዓቱ ታዳሚያን መካከል የዘፈን ምርጫን በተመለከተ የነበረ አለመግባባት ነው።

ያንንም አለመግባባት በመያዝ ምረቃው ተከናውኖ ምሽት ላይ ከውስጥም ከውጭም የነበሩ ልዩነቱን ይዘው ወደ መጣላት እና ግጭት ማምራታቸውን፤ በዚህም ወቅት በሁለት አርቲስቶች ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።

በሰዓቱም ፖሊስ በስፍራው በመድረስ ግጭቱን በማሰቆም ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረጉን አስረድተዋል።

አስተዳደሩም ጉዳቱን ማን እንዳደረሰ የፖሊስ ቡድን አዋቅሮ እየመረመረ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ከዚህ ውጭ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለ ጉዳቱ፣ ሰዎች ታስረዋል እና ፖሊስ ጉዳት አደረሰ ተብሎ የሚወራው ሀሰት መሆኑን እና የታሰረ ሰው እንደሌለ፤ የፖሊስም ሚና ግጭቱን የማስቆም እና ጉዳት እንዳይደርስ የማድረግ ብቻ እንደነበረ አረጋግጠዋል።

አሁን ላይ ከተማዋ ፍፁም ሰላማዊ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝም ነው የገለፁት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.