Fana: At a Speed of Life!

በቢሾፍቱ ከተማ በ28 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ብሄራዊ የጤፍ ምርምር ቤተ ሙከራ ተመረቀ

አዲስ አበባ ፣መስከረም 27 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ በቢሾፍቱ ከተማ የተገነባው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ብሄራዊ የጤፍ ምርምር የቤተ ሙከራ ህንፃ ተመረቀ።

28 ሚሊየን ብርና ሶስት አመታትን የፈጀው ማዕከል ለተሟላ የምርምርና ጥናት ዘርፍ ተቋሙ ሊያሟላ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ጫንያለው ጠቁመዋል።

የብሄራዊ ጤፍ ምርምር ማእከሉ በሚፈለገው የምርምር እና ጥናት አቅም ለመምራት የመሬት ጉዳይ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥና ማነስ እንዲሁም የጎርፍ ችግርን የሚመለከተው አካል በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተገልጿል።

በምርቃት ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ህንፃውን ገንብቶ ማስመረቅ በራሱ ግብ ሳይሆን በውስጡ በተለይም በጤፍ ዘርፍ የሚሰሩ የምርምር ስራዎችን መደገፍና በአርሶ አደሩ ዘንድ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መሰራት እንዳለበት መልእክት አስተላልፈዋል።

ለብሄራዊ ጤፍ ምርምር ቤተ ሙከራው መገንባት ድጋፍ ላደረጉ ተቋሟት እና ግለሰቦች በፕሮግራሙ እውቅና መሰጠቱን ኢቢሲ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.