Fana: At a Speed of Life!

በባህር ዳር ከተማ ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ የሆኑ የተለያዩ ምርቶች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 16 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በባህር ዳር ከተማ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የታሸጉ ምግቦችና ሌሎችም ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ የሆኑ ምርቶች መያዛቸውን በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ቆየ ÷ በከተማዋ ለሦስት ቀናት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ግማሽ ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የታሸጉ ምግቦች፣ መጠጦች፣ የመዋቢያና ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ ያልተፈቀዱ የሲጋራ ምርቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
ከአነስተኛ ሱቅ እስከ ትላልቅ ሱፐር ማርኬቶችና ሆቴሎች ለሽያጭ ቀርበው የተገኙት እነዚህ ምርቶች ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ መሆናቸው በጤና ባለሙያ መረጋገጡንም አመልክተዋል።
ከእነዚህ ውስጥ የህፃናት ምግቦችና የዱቄት ወተት፣ ለስላሳ መጠጦች፣ የለውዝ ቅቤ፣ የመዋቢያ ቅባቶች፣ ያልተፈቀዱ የሲጋራና ሌሎችም ምርቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ሃላፊው አያይዘውም የታሸጉ ምግቦች ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩና ጣዕም እንዲሰጡ በሚል የሚጨመሩ የተለያዩ ኬሚካሎች ለጤና ጠንቅ የመሆን እድላቸው ሰፊ እንደሆነ ጠቁመው÷ ምርቶቹን በአብዛኛው የሚጠቀሙ ህፃናት፣ እናቶች፣ በዕድሜ የገፉና በህመም ላይ የሚገኙ ሰዎችን ለከፍተኛ የጤና ጉዳት እንደሚያደርጉም አስረድተዋል፡፡
የተያዙት ምርቶች አካባቢን በማይበክል መልኩ እንደሚወገዱም አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የምግብ ደህንነትና ኃይጅን ባለሙያ አቶ ሳሙኤል ከሃሊ በበኩላቸው÷ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦችና መድኃኒቶች ተሰራጭተው በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡን ለከፋ ጉዳት የሚዳርጉት እንደ ስኳር፣ ካንሰር እና ግፊት የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምንጫቸው የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸው እንደሆኑም ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ የራሱን ጥንቃቄ ከማድረግ ባለፈ ገላጭ ፅሑፍ የሌላቸውንና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች እንዳይገዛና መሰል ምርቶች ሲያጋጥሙትም በአቅራቢያው ለሚገኙ ተቆጣጣሪ አካላት እንዲጠቁም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.