Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኢንቨስትመንት የተሠማሩ ባለሃብቶች ውጤት ማስመዝገብ ጀምረዋል- አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይም ከለውጡ ወዲህ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች በተገቢው መንገድ እያለሙ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ በአቶ በላይነህ ክንዴ እየለማ የሚገኘውን የሠሊጥ እና አኩሪ አተር የኢንቨስትመንት ማሳ ጎብኝተዋል።

በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሠማሩት አቶ በላይነህ ክንዴ፣ በጉባ ወረዳ ከ2 ወራት በፊት በጀመሩት የእርሻ ልማት 150 ሄክታር አኩሪ አተር እና 250 ሄክታር ሠሊጥ በድምሩ 400 ሄክታር መሬት ማልማታቸውን ተናግረዋል።

ምርቱንም በአማራ ክልል ቡሬ ከተማ ለሚገኘው የዘይት ፋብሪካቸው በግብዓትነት እንደሚጠቀሙት የገለጹ ሲሆን፥ በቀጣይም በአካባቢው ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

እርሻ ልማቱ በአካባቢው ለሚገኙ 36 ቋሚና 38 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ነው የገለጹት።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፥ በተለይም ከለውጡ ቀደም ባሉት ዓመታት በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ስም ሠፋፊ የእርሻ መሬት ወስደው እና የባንክ ብድር ወስደው ወደልማት ሳይገቡ የቆዩ በርካታ ባለሃብቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ከለውጡ ወዲህ ግን በተለይም በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት በተወሰደው እርምጃ ክልሉ አልሚ ባለሃብቶችን ብቻ በመጋበዝ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።

በ2012 ዓ.ም በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ለመሠማራት ፈቃድ ጠይቀው ወደሥራ ከገቡት ውስጥ አቶ በላይነህ ክንዴ አንዱ መሆናቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በሁለት ወራት ውስጥ ሠሊጥ እና አኩሪ አተር በስፋት ማልማት መቻላቸው አስደሳችና ለሌሎችም ትምህርት እንደሚሆን አንስተዋል።

የክልሉ መንግስት በተገቢው መንገድ የሚያለሙ መሠል ባለሃብቶችን ለመደገፍ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሆነ መግለፃቸውንም ከክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.