Fana: At a Speed of Life!

በብልፅግና ጉዞው ባለሃብቶች የማይተካ ሚና አላቸው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ባለሃብቶች ቀን በክልሉ መንግስት በውይይት እየተከበረ ነው።

በውይይት መድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች ተገኝተዋል።

ውይይቱ በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ባለሃብቶች ክልሉ ያለውን እምቅ አቅምና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በብልፅግና ጉዞው የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱት ባለሃብቶች ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ የማይተካ ሚና እንዳላቸውም አውስተዋል።

በሌላ በኩል ባለሃብቶች በአቋራጭ ለማደግ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የራሳቸውን ሰው በመወከል የሚያከናውኑትን ህገ ወጥ አሰራርም ኮንነዋል።

መሰል አሰራሮች መቆም አለባቸው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ባለሃብቶች የሚገጥማቸውን ማንኛውም ችግር ለመንግስት በመጠቆም በጋራ መፍትሄ እንዲሰጥባቸው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከተለመደው አሰራር በመውጣት መንግስትንም ሆነ ባለሃብቱን ተጠያቂ የሚያደርግ ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የግሉን ዘርፍ ለማነቃቃት በተያዘው የመንግስት እቅድ መሰረት የስራ እድልን በመፍጠር ረገድ ባለሃብቶች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አስታውሰዋል።

በውይይቱ የክልሉ ኢንቨስትመንት ያለበት ደረጃና እድሎችን የዳሰሰ የጥናት ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን፥ በየዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ውጤትን መሰረት ያደረገ የማሌዥያ ተሞክሮ ቀርቧል።

በክልሉ ባለፉት 20 አመታት ከተጀመሩት 10 ሺህ በላይ ኢንቨስትመንቶች በስራ ላይ የሚገኙት 60 በመቶ እንደማይሞሉና የፈጠሩት የስራ እድልም ከታቀደው 50 በመቶ እንደማይሞላ ተገልጿል።

ባለሃብቶች በበኩላቸው በስራ ሂደት ላይ የሚስተዋሉ የአሰራር አቅርቦትና ድጋፍ ጋር የተገናኙ ችግሮችን ያነሱ ሲሆን፥ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነትም አሳይተዋል።

በሀብታሙ ተክለስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.