Fana: At a Speed of Life!

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የተገነቡ 2 ሺህ 700 ቤቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የተገነቡና 2 ሺህ 700 ሰራተኞችን የሚያስተናግዱ የመኖሪያ ሕንፃዎች ተመረቁ፡፡
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኙ አምራች ኩባንያዎች መካከል ሺንትስ የተሰኘው የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ በ10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የገነባቸውና 2 ሺሕ 700 ሰራተኞችን የሚያስተናግዱት የመኖሪያ ህንፃዎች በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ፥ መንግስት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አምስት ዋና ዋና ሴክተሮች አንዱ አምራች ኢንዱስትሪው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በ2030 በአምራች ኢንዱስትሪው ሴክተር ላይ የ20 ነጥብ 6 በመቶ እድገት እንዲመዘገብ እንደሚጠበቅ ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው በዚህም አማካኝነት ከ1ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የስራ እድል በየዓመቱ ለመፍጠርም እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ኩባንያው ያከናወነው ስራ ለሌሎች መሰል ኩባንያዎች ምሳሌ እና አርዓያ ሆኖ መጠቀስ የሚችል ነው ያሉት አቶ ሳንዶካን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የአጭር ግዜ ታሪክ ውስጥ ሺንትስ ለሰራተኞቹ የመኖሪያ ቤት የገነባ የመጀመሪያው ኩባንያ ነው፤ ይህንንም ሌሎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች በአርዓያነት ሊከተሉ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.