Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ አካባቢዎች ለፖለቲካ ፓርቲዎች የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለፖለቲካ ፓርቲዎች የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ በጎንደር ከተማ፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች በሚገኙ የወረዳ ከተሞች፣ በኮምቦልቻ ከተማ፣ በጉራጌ ዞን የቸሃ ወረዳና የእምድብር ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በጎንደር ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የከተማዋ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች እና የፓርቲው አባላት ተገኝተዋል።

በድሬዳዋ ከተማ በተደረገው የድጋፍ ሠልፍ የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ እና የድሬደዋ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መብራቴ ገ/የስ ጨምሮ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።

በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የፓርቲው አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)በደብረብርሃን ከተማ፣ በእነሞር እና ኤነር ምርጫ ወረዳ በወይራ እና ሚቄ፣ ጉንችሬ ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ አድርጓል።

ለአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የድጋፍ ሰልፍ በፍኖተ ሰላም ከተማ የተካሄደ ሲሆን፥ ፓርቲው በደብረ ታቦር ከተማ ባካሄደው መድረክ ለምርጫ 2013 ያዘጋጀውን ማኒፌስቶ ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ አስተዋውቋል።

በፍኖተ ሰላም ከተካሄደው ሰልፍ ባሻገርም አብንን ወክለው ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ እጩዎችን ለማስተዋወቅ ከደጋፊዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጥቂት ቀናት በቀሩት የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራም ፓርቲዎች የማጠቃለያ የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.