Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ምሁራን ለሃገር የመቆም ጥሪ አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ምሁራን ለሃገር የመቆም ጥሪ አስተላለፉ፡፡

ምሁራኑ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያና በአፍሪካ የሚገኙ 70 የሚደርሱ ሲሆን፥ ባስተላለፉት ለሃገር የመቆም ጥሪ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በረጅም እድሜዋ ብዙ ጊዜ ታማ መዳኗን ጠቅሰዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ልጆቿ አልፎ አልፎ ተጣልተዋል፤ ተዋግተዋልም፤ ግን በጠባቸው መካከል እንኳን ለሃገራቸው ተባብረዋል እንጅ ምንጊዜም ሕልውናዋን ለጠላት አሳልፈው ሰጥተዋት አያውቁም” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን የውጭ ጠላቶች በተለያየ ጊዜ ሊደፍሯት ሞክረው ሁሉም አፍረው መመለሳቸውንም በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

በዚህም ለሌሎች የነጻነት ምሳሌ ሆና መኖሯን ጠቅሰው፥ ስለዚህም ኢትዮጵያ በነፃነቷ ቆማ፣ በኩራት ከትውልድ ወደ ትውልድ መተተላፏንም ገልጸዋል፡፡

“በአሁኑ ጊዜ ያለው ተቀዳሚ ቅራኔ ኢትዮጵያ ትፍረስ በሚሉና አትፈርስም በሚሉ መካከል ያለ ፍልሚያ ነው” በማለትም “አደገኛ የውስጥ ግጭትና የውጭ ከበባና ዛቻ ባለበት በዚህ ወቅት ልዩነት ላይ በማተኮር የምንበታተንበት ሳይሆን የተነሳብንን አደጋ በጥልቀትና አርቆ በማሰብ መርምረን በምን መልክ እንመክታለን በሚለው ላይ ተቻችለን መተባበር ነው” ሲሉ ምሁራኑ ባወጡት የጋራ መግለጫ ጥሪ አስተላልፈዋል።

“የውስጥ ቅራኔዎችን ትልቁን የሕልውና አደጋ ካሸነፍን በኋላ እንደርስባቸዋለን ብለን እናምናለን” ነው ያሉት በመግለጫቸው፡፡

በዘመናት የተፈጸሙ የአፍርሶ መገንባት ስህተቶችን መድገም የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል ያሉት ምሁራኑ፥ ሁሉም ነገር ሊታሰብና ሊተገበር የሚችለውም ኢትዮጵያ ስትኖር ብቻ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.