Fana: At a Speed of Life!

በተመድ ምክትል ዋና ፀሀፊ የተመራ የመንግሥቱ ድርጅት ልኡክ ኮምቦልቻ ከተማ የጅምላ መቃብር ቦታንና በሽብር ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ የተመራ የመንግሥቱ ድርጅት ልኡክ በኮምቦልቻ ከተማ የጅምላ መቃብር ቦታንና በሽብር ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን ጎበኘ፡፡

ዛሬ ረፋድ ኮምቦልቻ ከተማ የገባው በምክትል ዋና ፀሀፊዋ አሚና መሀመድ የተመድ ልኡካን ቡድን የሽብር ቡድኑ ህወሃት ሰለባ የሆኑ ከተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍል የተዉጣጡ አካላትን አግኝተዋል ።

አስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈፀመባቸውን ሴቶችንና በጦርነቱ በግፍ ወላጆቻቸውን ያጡ ተማሪዎችንም አግኝተዋል ፤የኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክን የጎበኙት ምክትል ዋና ፀሀፊዋ የሽብር ቡድኑ ህወሀት በኮሌጁ ላይ ያደረሰዉን ዉድመት እና በግፍ ገድሎ በጅምላ የቀበረበትንም ቦታ ተመልክተዋል ።

በነበረው ውይይት የሽብር ቡድኑ ይዟቸዉ በነበሩ 7ት ዞኖች የደረሱ ቁሳዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳቶች እንዲሁም የግፍ ግድያን በምስል ማስረዳት ተችሏል ያሉት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ጌታቸዉ ጀንበር በክልሉ የደረሰዉን ሰፊ ጥፋት ጥቂት ማሳያዎች መነሻ በማድረግ ለልኡካኑ ማሳየት መቻሉን ተናግረዋል ።

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን በህዝቡ ላይ በሽብር ቡድኑ የተፈፀመን በደል ማስረዳት መቻሉን አንስተዋል ።

የተመድ ልኡካን የጎበኙትና በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰበት እና የጅምላ መቃብር ተፈፅሞበታል የተባለዉ የኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን መላኩ አራጋዉም÷ የሽብር ቡድኑ ኮሌጁን እና መሰል ተቋማትን ያነጣጠረዉ ጥቃት ኮምቦልቻ እና አካባቢዉ አልሞ የተፈፀመ ብቻ ሳይሆን ተቋሙ የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል የመሆን እንቅስቃሴዉን ተከትሎ ሀገርን እና ሊመጣ የሚችልን ቃጠናዊ ትስስርን መጉዳት አስቦም የተፈፀመ ስለመሆኑ ነዉ የተናገሩት ።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ በጉብኝታቸዉ የደረሱ ዉድመቶችን ተመልክተዉ የሰላምን ዋጋ ያዩበት እንደሆነ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል ወደሰላም እዲመለስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።

በቀጣዮቹ ቀናት የትግራይ ክልልን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችን ይጎበኛሉ ተብለዉ የሚጠበቁት ም/ዋና ፀሀፊዋ አሚና መሀመድ ከነገ በስተያ ባሉት ቀናት የጉብኝታቸዉን ማጠቃለያ የተመለከተ ይፋዊ መግለጫን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

በፀጋዬ ወንደሰን

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.