Fana: At a Speed of Life!

በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ የንግድና መጠጥ ቤቶችን ተጽዕኖ ለመከላከል እየተሰራ  ነው- የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ የንግድና መጠጥ ቤቶችን ተጽዕኖ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡

ትምህርት ቢሮው “በመልካም ስብእና የታነፁ” ተማሪዎችን ለማፍራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል  በጋራ ለመስራትም ስምምነት ተፈራርሟል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ሻንቆ በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍራት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“በዚህም በትምህርት ተቋማት አካባቢ የመማር ማስተማር ሂደት የሚያውኩ የንግድ፣ መጠጥ ቤቶችና መሰል ተቋማትን ተጽዕኖ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው” ብለዋል።

መልካም ስብዕና ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት የወላጆች፣ የትምህርት ተቋማት፣ መምህራንና ሌሎችም አካላት ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ ተግባራትን ለመከላከል፣ ተማሪዎችን ለአጓጉል ተግባራት እንዳይጋለጡና ብቃትና መልካም ስነ ምግባር የተላበሰ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል የጋራ የመግባቢያ ስምምነትም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተፈራርሟል።

እንደ ኤዜአ ዘገባ ቢሮው ስምምነት ከተፈራረማቸው መካከል የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ አገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲና የከተማ አስተዳደሩ ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ይገኙበታል፡፡

የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ድንቅዓለም ቶሎሳ ÷ማህበራቸው በመማር ማስተማር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማቃለል በተዘጋጀው ስምምነት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም ወላጆች ልጆቻቸው ከትምህርት ቤት በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲወጡ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ነገሮችን ለማስቆም ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ተማሪዎችን የሚያውኩ የንግድ ፈቃዶች መሰጠት እንደሌለባቸውም አንስተዋል።

ከሌሎች የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራትም ወሳኝ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.