Fana: At a Speed of Life!

በትምህርት ተቋማት የሚታዩ የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታየውን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተገለፀ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሮችና የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት፣ ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትናንትናው እለት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲን የስራ እንቅስቀሴ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ዩኒቨርስቲው በትምህርት ዓመቱ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎችን ብቻ በመለየት ወደግቢው የሚያስገባ የዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ ማድረጉን ተመልክተዋል።

ቴክኖሎጂው ተማሪዎች ወደ መመገቢያ አዳራሽ ሲገቡም ጥቅም ላይ እንደሚውል በተግባር የተመለከቱት የኮሚቴው አባላት፥ ቴክኖሎጂውን ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በማስፋፋት ለተለየ ተልዕኮ ተመሳስለው የሚገቡ አካላትን መከላከል ይቻላል ብለዋል።

ስለሆነም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታየውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደአንድ መፍትሄ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።

ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ወደግቢው የሚገቡትን ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችን መለየት ይቻላል ያሉት የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ፥ ቴክኖሎጂው ከሬጅስትራር ጀምሮ የተሳሰረ በመሆኑ የተማሪዎችን ወቅታዊ የትምህርት ሁኔታ በቀላሉ ለማወቅ ይቻላል ብለዋል።

በቆይታቸው የስፔስ ሳይንስን ጨምሮ የዩኒቨርስቲውን የልህቀት ማዕከላት፣ የስታዲየሙ ግንባታ ያለበትን ደረጃ፣ ቤተመፃህፍት፣ ማተሚያ ቤት፣ የሴቶች መኝታ ክፍሎችን፣ ቤተሙከራ፣ ክሊኒክ እና ሌሎችንም ጎብኝተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እምዬ ቢተው እንዳሉት፥ በዩኒቨርስቲው መውጣትና በህብረተሰቡ መታየት ያለባቸው ለሌሎች ዩኒቨርስቲዎች አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ስራዎች እንዳሉት አይተናል።

ዩኒቨርስቲውም ያለውን ምርጥ ተሞክሮ ቀምሮ ወደሌሎች የማስፋፋት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበከሉላቸው፥ ዩኒቨርስቲዎች ለሀገሪቱ መሻሻል ብዙ ጥረቶችን ያደርጋል፤ እነዚህንም ጥረቶች ለማስቀጠል ማንኛውም አደናቃፊ ሁኔታ መላ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።

አያይዘውም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለማስተካከልም ሚኒስቴሩ እየሰራ መሆኑን መግለፃቸውንከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስተር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.