Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ለተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ተጠያቂው ህወሓት ነው – የተመድ የልማት ፕሮግራም ሰነድ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ሰብዓዊ ኪሳራና አለመረጋጋት ኃላፊነቱን የሚወስደው ትግራይን ሲመራ የነበረው ህወሓት እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ለድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጻፈው ማስታወሻ ይፋ አደረገ።

ማስታወሻውን ይፋ ያደረገው ፎሬይን ፖሊሲ የተሰኘው መጽሄት ነው፡፡

የተመድ የልማት ፕሮግራም አስተዳዳሪ አቺም ስቴይነር በምስራቅ አፍሪካ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲፈጠር ያደረገው ኢትዮጵያን ላለፉት 30 ዓመታት ያህል ሲመራ የነበረው  የህወሃት አመራር መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡

አመራሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የሰሜን ዕዝ ንብረቶችን ለመቆጣጠር ያለመ እንቅስቃሴ እንደነበረ ነው ያስረዱት፡፡

ይህንንም ተከትሎ የትኛውም ሉዓላዊ ሀገር ጥቃት ሲዘነዘርበት አጸፋዊ ምላሽ ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን ማድረጋቸውን በማስታወሻቸው የጠቀሱት  የተመድ የልማት ፕሮግራም አስተዳዳሪ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተሳሳተ መንገድ በመረዳቱ ኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል፡፡

ለጋሾችና የመብት ተማጋቾች ሁኔታውን ከማስጮህ ተቆጥበው በመልሶ ማልማትና በሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ ስለማቅረቡ የተነገረለት ማስታወሻው፤ “ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መሪነትና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተሳትፎ ሊጣሩ ይገባል” ብሏል።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ወደ አንድ ወገን ያጋደሉ ሰብአዊ መብቶችን የተመለከቱ ዘገባዎች ግጭቱን ከማባባስ ባለፈ አፍራሽ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችልም ማስታወሻው አስጠንቅቋል።

የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ህወሃት በደረሰበት ሽንፈት ከ10 ሺህ በላይ የወንጀል እስረኞችን ከማረሚያ ፈትቶ በመልቀቅ የትግራይ ክልል ለአስተዳደር እንዳይመች ብሎም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲፈጸሙ ወንጀሎችና ግድያዎች እንዲበራከቱ ስለማድረጉም ማስታወሻው ዘርዝሯል።

የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመንግስት ሰራተኞች ውዝፍ ደመወዝ በመክፈል የባንክ የቴሌኮምና የመብራት አገልግሎቶች ዳግም ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረጉን አትቷል።

ማስታወሻው የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ለእርዳታ ሰጪዎችና ለአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት አካባቢው ዝግ ሆኖ እንዲቆይ ስለመደረጉ አስታውሶ፤ የህግ ማስከበር ዘመቻው በመጠናቀቁ የኢትዮጵያ መንግስት ለጋሾችና ጋዜጠኞች ወደ አካባቢው መሄድ እንደሚችሉ ቢፈቅድም የድርጅቶቹ ሰራተኞችና ጋዜጠኞች የተሳሳቱና የተዛቡ መረጃዎችን አሁንም እያሰራጩ እንደሚገኙ ገልጿል።

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.