Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን የሚያግዙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርጉ 1 ሺህ 100 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተመረቁ።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰላም ሚኒስትር ጋር በመተባበር ለአንድ ወር ያሰለጠናቸውን በጎፈቃደኛ ወጣቶችነው ያስመረቀው።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ፤ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለችግር ለተጋለጡ የክልሉ ህብረተሰብ ክፍሎች  የተለያዩ ድጋፍ በማድረግ ወገናዊነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል።

ሰልጣኞቹ የተለያዩ ተፅእኖዎችን በመቋቋም ወደ ስልጠናው መምጣታቸውን የገለጹት ዶክተር ሙሉ ወጣቶቹ ህብረተሰቡን ካጋጠመው ችግር ለማውጣት እየተደረገ ባለው ጥረት ያቅማቸውን ለማበርከት በመወሰናቸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።

በጎ አገልግሎት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም በስፋት እንደሚሰራበት የተናገሩት ዶክተር ሙሉ ወጣቶች ህብረተሰቡን ለማገልገል በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ለቀጣይ ህይወታቸው መሰረት እየጣሉ መሆናቸውን አውቀው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

ሰልጣኝ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ለአስር ወራት በየአካባቢያቸው ተሰማርተው በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ዶክተር ሙሉ አስታውቀዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስማ ረዲ በበኩላቸው፤ ለአሁኑ የተመራቂ ወጣቶች የተሰጠው ስልጠና ተቋማቸው በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ  ስራ አካል መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለአንድ ወር ያህል በመቀሌ ዩኒቨርስቲ በተሰጠው ስልጠና ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተውጣጡ  1 ሺህ 100 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሳተፋቸውን  ዳሬክተሯ  አሰታውቀዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው  ስለ በጎ ፈቃደኝነት ምንነትና አስፈላጊነት፣  ስለ ስራ አመራር አስተዳደር፣ የስራ ፈጠራ ክህሎትና በሽርክና የመስራት አስፈላጊነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች  ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን አመልከተዋል።

ሰልጣኞች  የማንኛውም  የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው ስለመሆናቸው የስልጠናው አስተባባሪዎች አስታውቀዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.