Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ‘ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ አይደለም’ የሚሉ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አስበው ነው – ዶክተር ሙሉ ነጋ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ እንዳልሆነ የሚናገሩ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አስበው ነው ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ተናገሩ።
ዶክተር ሙሉ ነጋ ከኢዜአ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን ሲጀምር ለዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ትኩረት አድርጎ ነው።
ነገር ግን የሰብአዊ ድጋፍ ስርጭቱ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይደርስ የጥፋት ቡድኑ እንቅፋት እንደነበረ አስታውሰዋል።
የጥፋት ቡድኑ የጭነት ተሽከርካሪዎችን አውድሞና የቀሩትን ይዞ መጥፋቱን ጠቅሰዋል።
አርሶ አደሩ እህል በሚያጭድበትና በሚሰበስብበት ወቅት የጥፋት ቡድኑ ችግሩን በመፍጠሩም ለሰብዓዊ ቀውሱ መባባስ አንድ ምክንያት መሆኑንም አውስተዋል።
በጥፋት ቡድኑ ምክንያት ህዝቡ ያለ መብራትና ውሃ በመቆየቱ ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል ያሉት ዶክተር ሙሉ÷ የፌደራል መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ እንዳልሆነ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬም ከእውነት የራቀ መሆኑንም ነው የገለጹት።
‘ድጋፉ እየቀረበ አይደለም’ በሚል ሃሰተኛ መረጃ የሚያናፍሱ አካላት የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ የሚፈጽሙት ድርጊት እንደሆነም ጠቁመዋል።
በክልሉ የመብራት፣ የውሃ እና የባንክ አገልግሎቶች በበርካታ አካባቢዎች መጀመራቸውን አንስተው÷ አገልግሎት ባልተጀመረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ደመወዝ ላልተከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች እንዲከፈላቸው እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የትግራይ ክልልን መልሶ በመገንባት ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ዶክተር ሙሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.