Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች ድጋፉ ተጠናክሮ ቀጥሏል – ዶክተር ሙሉ ነጋ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) በትግራይ ክልል አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ካቢኔ አወቃቀርም በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት የሚገፋ ቡድን ወይም ግለሰብ እንደማይኖር ማረጋገጡን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፌደራሉ መንግስት ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸው ይታወሳል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ÷ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ በርካታ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን በጀመረበት ወቅት የታጠቁ ግለሰቦችን ትጥቅ ማስፈታት፣ የተቋረጡ ህዝባዊ አገልግሎቶችን ማስጀመርና የክልሉን ካቤኔ አዋቅሮ ወደ ስራ ማስገባት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱንም ነው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በፈቃዳቸው ትጥቃቸውን ለጸጥታ አካላት እያስረከቡ ይገኛሉ ያሉት ጊዜያዊ ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ሸሽተው የነበሩ ሚሊሻዎችም ትጥቃቸውን አስረክበው በሰላም ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በወንጀል የማይፈለጉ የመንግስት ሰራተኞችም ወደ ስራ ገበታቸው መመለሳቸውን ጠቁመው ÷የክልሉ ካቢኔም በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ባቀፈ መልኩ መዋቀሩን ገልጸዋል።
የካቢኔ አወቃቀሩም ከዚህ በኋላ በትግራይ ክልል በአመለካከቱ ምክንያት የትኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን መገፋት እንደሌለበት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የመንግስት አገልግሎትና የፖለቲካ ፓርቲ የተለያዩ መሆናቸውን በተግባር ማሳየቱን ዶክተር ሙሉ ጠቁመዋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳር አባላት በተለያዩ አካባቢዎች በተንቀሳቀሱበት ወቅት ጁንታው በመሰረተ ልማቶች ላይ እጅግ አሳፋሪ በሆነ መልኩ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ መታዘባቸውንም ነው የተናገሩት።
በተለይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጡ መስመሮች በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳታቸው ህዝባዊ አገልግሎቶችን በሁሉም አካባቢ በፍጥነት ማስጀመር አልተቻለም ነው ያሉት።
የፌደራል መንግስት ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ ከደቡብ ትግራይ ጀምሮ እስከ አዲግራት ድረስ የመብራት አገልግሎት ማስጀመር ማቻሉን ገልጸዋል።
በቀጣይም አገልግሎቱን በሁሉም አካባቢ ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ዶክተር ሙሉ አያይዘውም በውይይት መድረኮች ላይ ተሳታፊዎቹ ያለምንም ገደብ ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ መቻላቸውንም ተናግረዋል።
በክልሉ የአፈና ስርዓት ተንሰራፍቶ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ የውውይት መድረኮቹ አዲስ የነጻነት አየርን ያለማመዱ እንደነበርም ነው የጠቆሙት።
የትግራይ ክልልን መልሶ በማቋቋም ረገድ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰብአዊ ድጋፎች በሁሉም ቦታ ተደራሽ እንዲሆኑ የማጓጓዝ ስራ እያከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
የፌደራል መንግስቱ ከአስቸኳይ ድጋፍ በተጨማሪ ከበጀት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.