Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ከአንድ ሚሊየን የሚበልጡ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ሊጀመር ነው 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)በትግራይ ክልል ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ከአንድ ሚሊየን የሚበልጡ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አምስተኛው ምዕራፍ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ።

የልማታዊ ሴፍቲኔት የአምስተኛ ምዕራፍ መረሃ ግብር በክልሉ ለመጀመር የሚያስችል የትውውቅ መድረክ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተካሄዷል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚን ወሃብረቢ ÷አምስተኛው ምዕራፍ በትግራይ ክልል የሚጀመረው ህዝቡን ካለበት ችግር እንዲወጣ ለማስቻል ታቅዶ የሚካሄድ ነው።

ይህም ክልሉ ወቅታዊ ችግር ባለበት ሁኔታ የሚጀመር ቢሆንም ያለው ክፍተት ለመሙላት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ በክልሉ 55 ወረዳዎች ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለሚካሄደው የሴፍቲኔት ፕሮግራም 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መመደቡን ሚኒስቴር ዴኤታዋ አስታውቀዋል።

በሴፍቲኔት ፕሮግራሙ የሚታቀፉ ዜጎች በተፈጥሮ ሃብትና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች በማሳተፍ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የተዘጋጀ ዕቅድና ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚቆይ መሆኑን አስረድተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው÷ በሀገሪቱ ቀደም ባሉት ዓመታት በፕሮግራሙ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በተካሄዱ ስራዎች የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም በተለያዩ ወቅቶች በሀገሪቱ ይከሰት የነበረውን ድርቅ ለመቋቋም ማስቻሉን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ምዕራፎች በፕሮግራሙ ከታቀፉት ወገኖች ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚሆኑት የምግብ ዋስትና በማረጋገጣቸው ተመርቀው መውጣታቸው ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

አምስት ሚሊየን በሚጠጋ ህዝብና በተወሰኑ ወረዳዎች ሲካሄድ የቆየው ይሄው ፕሮግራም በአሁኑ ወቅት እየሰፋ መምጣቱን አስረድተዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አበበ ገብረህይወት÷ ክልሉ ከደረሰበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማውጣት በሚደረገው ጥረት የፕሮግራሙ መጀመር  የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።

የሴፍቲኔትና ሌሎችም የልማት ፕሮግራሞች ተፈጻሚ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት በየደረጃው ያሉት አመራሮች ከህዝቡ ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በፕሮግራሙ ያልተካተቱንም በመጨመር  ውጤታማ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ አድርገን ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀሰ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የአምስተኛው ዙር የሰፍትኔት ፕሮግራም ዕቅድ ሲዘጋጅ አሁን ያለውን የትግራይ ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ የማህበራዊ ረድኤት ትግራይ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ገብረሚካኤል ናቸው።

ፕሮግራሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀ ቢሆንም በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተለየ መልኩ ለማስኬድ የደረሰውን ጉዳት የሚያስረዳ ጥናት መደረጉን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ያስሚን ወሃብረቢ አስረድተዋል።

በሀገሪቱ ባለፉት 20 ዓመታት መንግስት ሲያካሂደው የቆየው የድህነት ቅነሳ  ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን የሴፍቲኔት መረሃ ግብር የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጉን በመድረኩ መገለጹን ኢዚአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.