Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ከ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል ከ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የብሄራዊ አደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

በትግራይ ክልል ከተካሄደው ህግ ማስከበር እና ህልውና ዘመቻ መጠናቀቅ ማግስት ዜጎችን በተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎች መድረስ ቀዳሚ ትኩረት በአብዛኛው በሀገሪቱ መንግስት ቀሪው ደግሞ በተራድኦ ደርጅቶች መቀጠሉ ተገልጿል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር የስልክ ቆይታ የነበራቸው የብሄራዊ አደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ÷ በጥቅሉ በትግራይ ክልል ብቻ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ለመድረስ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በቀጣይም እንደ ትግራይ ክልል እና ሀገር እየተደረገ ያለው ድጋፍ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር 10 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ ምርቶች ግዥ እየተፈጸመ ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ ለአመታት ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ያካበተችው ልምድ ሲታይ አሁን ላይ ያሉትን ችግሮች የመቋቋም ቁመና ላይ ናትም ነው ያሉት።

መቐለ የደረሰው ድጋፍ እስከ አዲግራት እና አካባቢዎቹ ላሉ ነዋሪዎች የሚደርስ ሲሆን÷ሽረ ላይ የደረሰውም ድጋፍ ቢሆን ከአክሱም እስከ አድዋ ብሎም ሽራሮን እና ሌሎችን አካባቢዎችን ማደረስ ያስችላሰል እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ።

ከዚህ ባለፈም አላማጣ የደረሰው ድጋፍ ኮረም ፣ ጨርጨር ፣ መኾኒ እና ሌሎችም አካባቢዎች ለመድረስ እንደ መሰላል ያገለግላል ነው የተባለው።

ከተለያዩ ተቋማት ጋር ዜጎችን የመደገፍ ተግባር የሚፈጽመው ኮሚሽኑ የትግራይን ክልል ከፊት አመጣን እንጂ ከአንበጣ እስከ ጎርፍ ከዚያም በግጭት እና በሌሎች ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉት እና ለችግር እጅ ለሰጡት ዜጎች ድጋፉን መቀጠሉን አንስተዋል።

በዚህም ከአማራ እስከ አፋር፣ ከቤኒሻንጉል እስከ ሌሎችም ክልሎች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በ2008 ኤልኒኖ ያስከተለው ድርቅ የ10 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎችን እጅ ለእርዳታ እንዲዘረጉ አድርጓቸዋል።

ይህ ደግሞ ባለፉት 50 ዓመታት የሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ያልተከሰተ እንግዳ ክስተት ነበር ነው ያሉት።

ይህም ሆኖ ግን አንድም ሰው ህይወቱ አላለፈም ነበር የሚሉት የብሄራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ÷ ለመርዳት እና መልሶ ለማቋቋም የሚከብድ ደረጃ ላይ አይደለንም ብለዋል።

በቀጣይ ከውጭ 10 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ እና ከሀገር ውስጥም የተለያዩ ምርቶችን ለመግዛት መንግስት በእንቅስቃሴ ላይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በአፈወርቅ አለሙ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.