Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች ጠግኖ ሁሉንም ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ እና በዙሪያው ባሉ ከተሞች ተቋርጦ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወደ መደበኛ አገልግሎት አሰጣጡ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ እየተሰራ እንዲያገኝ ተገለጸ።

በአሁኑ ወቅት ዋጃ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ማይጨው፣ መሆኒ፣ ዓዲጎሱ፣ አዲ ጉደም፣ ኩሓ፣ መቐለ፣ ውቅሮ፣ አጉላዕ፣ ዓዲግራት፣ ሓውዜን፣ አጉላዕ እና በአፋር ክልል የሚገኘው በርሃሌ ከተማም ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በተጨማሪም ፍረወይኒ፣ ዕዳጋ ሐሙስ፣ ዓብይ አዲ፣ ዛላንበሳ፣ ደውሃን፣ የጭላ፣ ሀገረ ሠላም እና አፅቢ በቅርብ ቀን ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች በትግራይ ክልል በአንዳንድ ቦታዎች በመዘዋወር የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ላይ ምልከታ አካሂደዋል።

ቡድኑ እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም የመስክ ምልከታ ያደረገባቸው የመቀሌ፣ ኩሂያ፣ ውቅሮ፣ አጉላ፣ ፍረወይኒ፣ እዳጋሀሙስ፣ ነጃሺ፣ አዲግራት ከተሞች የሚገኙ የአገልግሎቱ ሠራተኞችና ቢሮዎችን እንዲሁም በጥገና ስራ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን ጭምር በመጎብኘት ከማበረታታቱ ባሻገር ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች የለየ ሲሆን በቀጣይ ሊደረጉ የሚገባቸው ድጋፎችንም ለይቷል፡፡

ሠራተኛው በክልሉ በተፈጠረው ሁኔታ በመሠረተ ልማቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅንጅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ህብረተሰቡ የተቋረጠበትን ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆኑ በአካል በተደረገ የመስክ ምልከታ ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ጉዳት የደረሰበትን መስመር መልሶ በመጠገን ወደ ስራ ለማስገባት ተቋሙ ባለ 50 ኤሲ 45ሺህ ሜትር፣ ባለ 95 ኤሲ 9 ሺህ እና ኮምፖስድ ኢንሱሌተር የተባሉ ግብዓቶች ለክልሉ እንዲደርስ የተደረገ ቢሆንም ኔትዎርኩ ላይ ከደረሰው ጉዳት አኳያ በቀጣይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡

በመጨረሻም ስለ ነባራዊ ሁኔታና ቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ በመቀሌ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመገኘት ከማኔጅመንቱ ጋር የምክክር መድረክ በማድረግ ጉብኝቱን አጠናቋል፡፡

የህብረተሰቡን የኃይል ፍላጎት በአፋጣኝ ወደ ቀድሞው አገልግሎት ለመመለስ ሲሰሩ የቆዩ የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጥገና ክፍል ሰራተኛች የማኔጅመንት አባላት አድንቀዋል፡፡

ተቋሙ በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች ጠግኖ ሁሉንም የክልሉ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.